በጋምቤላ የወባ ወረርሽኝና የውሃ ወለድ በሽታዎች እንዳይከሰቱ ለመከላከል የተጀመረ የድጋፍ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል-ዶክተር ሊያ ታደሰ

173

ጋምቤላ መስከረም 25/ 2015( ኢዜአ) -በጋምቤላ ክልል ተከስቶ ከነበረው የጎርፍ አደጋ ጋር ተያይዞ የወባ ወረርሽኝና የውሃ ወለድ በሽታዎች እንዳይከሰቱ ለመከላከል እየተደረገ ያለው የድጋፍና ክትትል ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።

የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የጎርፍ አደጋ በተከሰተባቸው የኑዌርና የአኝዋሃ ዞኖች የመስክ ምልከታ አካሄደዋል።

ሚኒስትሯ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በክልሉ አስር ወረዳዎች ተከሰቶ ከነበረው የጎርፍ አደጋ ጋር ተያይዞ የወባ ወረርሽኝና የውሃ ወለድ በሽታዎች እንዳይከሰቱ በሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ድጋፍና ክትትል እያደረገ ነው።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የጎርፍ አደጋው ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ባለሙያዎችን በመመደብ ጭምር የወባና የውሃ ወለድ በሽታዎች እንዳይከሰቱ  ለመከላከል የሚያግዙ የመድኃኒት፣ የአጎበርና ሌሎች ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።

በቀጣይም በጎርፍ የተጎዱ የጤና ተቋማትን መልሶ ማደራጀትን ጨምሮ የተጀመሩ ሁሉን አቀፍ የድጋፍና ክትትል ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።

ሚኒስትሯ አክለው ጉዳቱ በደረሰባቸው አካባቢዎች ከፌዴራል ተቋማት ጋር የተደረገው ምልከታ የድጋፍና ክትትል ስራዎችን በተቀናጀ አግባብ ለማስኬድና ለችግሩ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

በተደረገው ምልከታም በክልሉ ተከስቶ የነበረው ጎርፍ እየቀነሰ መሆኑንና ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችም ወደ ቀያቸው መመለስ መጀመራቸውን መገንዘባቸውን ጠቅሰዋል።

"ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ የድጋፍና ክትትል ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል" ሲሉ  ሚኒስትሯ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዮት ዋና ዳይሬክተር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው በክልሉ የጎርፍ አደጋው ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ወደ አካባቢው የባለሙያዎች ቡድን በመላክ የድጋፍ ስራ ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ ከባለሙያ ድጋፍ በተጨማሪ የወባና የውሃ ወለድ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያግዙ 15 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የህክምና ግብዓቶችን ጨምሮ  ለስልጠና የሚውል የ4 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በክልሉ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ በተለይም ከጎርፍ ጋር ተያያዞ ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎችን ለመከላከል የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዮት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል ።

ህብረተሰቡ አሁንም በወባና በውሃ ወለድ በሽታዎች የመጋለጥ እድሉ ከፍተኛ ስለሆነ በሁለቱ ተቋማት የተጀመረው ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲጠናከር ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም