በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚከሰተውን ችግር ለመከላከል አገሮች በራሳቸው ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር በጋራ ሊሰሩ ይገባል ተባለ

12

መስከረም 25/2015/ኢዜአ/ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚከሰተውን ችግር ለመከላከል አገሮች በራሳቸው ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ።

በአለም በስፋት የተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ በተለያዩ አገራት ላይ ያልታሰቡና የማይገመቱ የተፈጥሮ አደጋዎችን በማድረስ የሰዎችን ህይወት ከመቅጠፍ ባለፈ በርካቶችን ከመኖሪያ ቀያቸው በማፈናቀል ለስደት ዳርጓቸዋል፡፡

ይህን የአለም ችግር ለመመከት ደግሞ በጋራ መስራት እንደሚገባ የተለያዩ አካላት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣል።

የአየር ንብረት ለውጥንና ችግሩን ለመከላከል በሚያግዙ ሀሳቦች ዙሪያ ትኩረቱን ያደረገ ውይይት ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

የካርቱም ሂደት -ሙያዊ ምክክር በሚል መሪ ሃሳብ የሚከናወነው ጉባኤ በአየር ንብረት ለውጥና ተያያዥ ችግሮች የሚከሰተውን ስደትና የሰዎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው መፈናቀልን ለመከላከል በሚረዱ ሃሳቦች ላይ እንደሚያተኩር ተገልጿል፡፡

አገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ተስማሚ የሆነ ኢኮኖሚ መገንባት፣ የሙቀት የልቀት መጠንን መቀነስ እና ሌሎች የመፍትሄ እርምጃዎችን ሊወስዱ እንደሚገባ ተጠቅሷል።

በአየር ንብረት ለውጥ የሚደርሰው ጉዳት ድንበር የማይገድበው ሲሆን የሙቀት መጨመር፣ የድርቅ እና የጎርፍ አደጋ፣ የበረዶ መቅለጥና የባህር ወለል መጨመርን የሚያስከትል መሆኑ ይታወቃል።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ፤ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የሚስማማ ኢኮኖሚ ለመገንባት የምታደርገው ጥረት ችግሩን ለመፍታት ጥሩ ምሳሌ ነው።

በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚከሰተውን ውስብስብ ችግር ለመከላከል አገሮች በራሳቸው ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር በጋራ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የጀመረችው ጥረት ለሌሎች አገራት ምሳሌ መሆን እንደሚችልም ጠቅሰዋል ።

በአረንጓዴ አሻራ እየተተገበረ የሚገኘው የችግኝ ተከላ፣ የታዳሽ ሃይል ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ስራ ለአየር ንብረት ለውጥ ተስማሚነት እየተሰራ መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል።

የበለጸጉ አገራት የሚያመነጩትን የካርቦን ልቀት ለመቀነስ መስራት እንዳለባቸው የጀርመን የውጭ ጉዳይ ቢሮ ተወካይና የአውሮፓ ስደተኞች ፖሊሲ ግብረሀይል ሃላፊ ማንፍሬድ ሹሩለር አሳስበዋል።

የበለጸጉ አገራት የሚለቁትን በካይ ጋዝ ተከትሎ የሚከሰተው ከፍ ያለ ሙቀት በተለይ በታዳጊ አገራት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን በመጠቆም ችግሩን ለመቅረፍ በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል።

በዓለም አቀፍ የስደተኞች ፖሊሲ ልማት ማዕከል የካርቱም ፕሮሰስ አስተባባሪ ሞኒካ ዜኔቲ በበኩላቸው ማዕከሉ በአየር ንብረት ለውጥና ስደተኞችን በተመለከተ ከአገራትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአየር ንብረት ለውጥና ስደት ዓለም አቀፍ ችግር በመሆኑ ጉዳቱን ለመቀነስ በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም