የኤሌክትሪክ ሃይል በመፍጠር የአካባቢውን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ያደረገው ታዳጊ የፈጠራ ስራው እንዲያድግና የባለቤትነት መብት እንዲያገኝ ይደገፋል- የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

130

መስከረም 25/2015/ኢዜአ/ በቦረና ዞን ከተለያዩ ነገሮች የኤሌክትሪክ ሃይል በመፍጠር የሚማርበትን ትምህርት ቤት ጨምሮ የአካባቢውን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ያደረገው ታዳጊየፈጠራ ስራው እንዲያድግና የባለቤትነት መብት እንዲያገኝ ድጋፍ የሚደረግለት መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ ተናገሩ።

የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በቦረና ዞን ዋጪሌ ወረዳ ዌብ ከተማ በመገኘት የዚህን ታዳጊ የፈጠራ ስራዎች ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝታቸውም ታዳጊው የተለያዩ ቁሶችን በመጠቀም በፈጠረው የኤሌክትሪክ ሃይል ከሚማርበት ቱላ ዌብ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተጨማሪ በዌብ ከተማ 37 መኖሪያ ቤቶች መብራት እንዲያገኙ ማድረጉንም ተመልክተዋል፡፡

ታዳጊው በዚህ ወቅት ለኢዜአ እንደገለጸው " ለፈጠራ ስራው ያነሳሳኝ በአከባቢዬ የመብራት አገልግሎት አለመኖር ነው" በማለት ተናግሯል፡፡

በተጨማሪም በአከባቢው የሚገኙ ተማሪዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከሚያገኙ ተማሪዎች ጋር እኩል ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግም ሌላኛው ለፈጠራ ስራው ያነሳሳው ምክንያት መሆኑን ተናግሯል፡፡

የፈጠራ ሥራውን እውን ለማድረግ ከዘጠኝ ጊዜ በላይ ተደጋጋሚ ሙከራ ማድረጉን አስታውሶ በ10ኛ ሙከራው የተሳካለት ሲሆን የሚማርበትን ትምህርት ቤት ጨምሮ የአካባቢውን ነዋሪዎች የመብራት ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።

የፈጠራ ሥራው አሁን ባለው ሁኔታ ያለምንም መቆራረጥ ለአምስት ወራት አገልግሎት እንደሚሰጥ የሚናገረው ተማሪ አዳን፣ ከፈጠራ ውጤቱም በወር እስከ 7 ሺህ ብር ገቢ እያገኘ መሆኑን ገልጿል።

የፈጠራ ውጤቱን ይበልጥ ለማሻሻል እና ከፍ ለማድረግ ሳይንሳዊ ሥልጠናዎችና መሳሪያዎችን የሚገዛበት ገንዘብ ድጋፍ እንደሚደረግለትም ጠይቋል፡፡

የቱላ ዌብ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ቦሩ ሶራ ከተማሪው የፈጠራ ውጤት ትምህርት ቤቱ በብዙ መልኩ ተጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።

በትምህርት ቤታቸው በማታው መርሃ ግብር የሚማሩ ተማሪዎችም ያለ አንዳች ችግር ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

የመብራት ተጠቃሚ የሆኑ የዌብ ከተማ ነዋሪ ኡቃ ቃሊቻ፤ በታዳጊው ፈጠራ መብራት በማግኘታቸው በእጅጉ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

የታዳጊውን የፈጠራ ስራ የጎበኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ፤ በፈጠራው መደነቃቸውን ገልጸዋል።

የኤሌክትሪክ ሃይል መቆጣጠር እንዲችልና ሃይሉም ከመብራት በተጨማሪ ለሌሎች አገልግሎቶች እንዲውል ድጋፍ ይደረግለታል ብለዋል፡፡

የታዳጊው ስራ የፈጠራ ባለቤትነት መብት እንዲሰጠውና ፈጠራውን እንዲያሳድግ ድጋፍ የሚደረግለት መሆኑን ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል፡፡  

በኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች ተደራሽ የማድረግ ራእይ ሰንቆ እየሰራ ያለው የ16 ዓመቱ ታዳጊ አደን ሁሴን ዲዳ በቦረና ዞን ዋጪሌ ወረዳ ዌብ ከተማ የ9ኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም