ኢትዮጵያ ለቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶች የሰጠችው ትኩረት ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ የሆኑ ዲጂታል መፍትሄዎችን ለማበጀት የሚያግዙ ናቸው-ፕሮፌሰር ቶሚ ሜየር

61

መስከረም 25/2015/ኢዜአ/ ኢትዮጵያ ለቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶች የሰጠችው ትኩረት ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ የሆኑ ዲጂታል መፍትሄዎችን ለማበጀት የሚያግዙ መሆናቸውን በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን ዩኒቨርሲቲ የኮምፒውተር ሳይንስ መምህርና የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል ተመራማሪ ፕሮፌሰር ቶሚ ሜየር ተናገሩ፡፡

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነው የፓን አፍሪካን አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጉባኤ አዲስ በተገነባው የሳይንስ ሙዚዬም ተካሂዷል፡፡

በጉባኤውም በዋናነት የአፍሪካ ችግሮችን ወቅቱን በዋጀና አፍሪካዊ በሆነ ዲጅታል አማራጭ መፍታት ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን፤ በመድረኩም ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የመጡ የዘርፉ ምሁራንና ተመራማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

በመድረኩ ጥናታዊ ጽሁፍ ካቀረቡ ምሁራን መካከል በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን ዩኒቨርሲቲ የኮምፒውተር ሳይንስ መምህርና የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል ተመራማሪ ፕሮፌሰር ቶሚ ሜየር እንዳሉት፤ አፍሪካውያን በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደገ ከመጣው የቴክኖሎጂ ዘርፍ ጋር አብረው ለመጓዝ መስራት አለባቸው፡፡

የቴክኖሎጂና የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ለነገ የሚተው ሳይሆን ዛሬ ተጀምሮ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚጎለብት ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡

በመሆኑም ህጻናትና ወጣቶችን ከወዲሁ በዘርፉ እየሰለጠኑ እንዲያድጉ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሙዚዬሞች ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው አብራርተዋል፡፡

ሌሎች አገራት ገብተው ቀጥታ በሚተገበሩ ቴክኖሎጂዎች የአፍሪካን ችግር በዘላቂነትመፍታት እንደማይቻልም ነው ያብራሩት፡፡

በመሆኑም ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ የሆኑ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስና ሌሎች ዲጂታል አማራጮች ያስፈልጉናል ነው ያሉት፡፡

ይህን እውን ማድረግ ደግሞ የአፍሪካ አገራት የቀጣይ የቤት ስራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ በአጭር ጊዜያት ወስጥ አርአያነት ያላቸው የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ግንባታዎችን እያከናወነች ስለመሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በተለይ ከተቋቋመ ሁለት ዓመታትን ብቻ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስትቲዩት በዘርፉ ያሉ አፍሪካዊያን ምሁራንና ተመራማሪዎች ተቀናጅተው እንዲሰሩ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዋና ዳይሬክተር ኢኒጂነር ወርቁ ጋቸና፤ ኢትዮጵያ የቴሌኮም መሰረተ ልማትን ጨምሮ ለቴክኖሎጂ ግንባታ የሰጠችው ትኩረት ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምቹ እድል የሚፈጥሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በአገር ውስጥ ያሉ ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማስፋፋት እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተለይ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መስክ ከአፍሪካ አገራት ጋር ተቀራርባ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗንም ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም