የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና የሎጂስቲክስ ዘርፍ አቅምን ለማሳደግና አሰራሩን ለማሳለጥ ስምምነት ተፈረመ

108

አዲስ አበባ መስከረም 25/2015 (ኢዜአ) የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና የሎጂስቲክስ ዘርፍ አቅምን ለማሳደግና አሰራሩን ለማሳለጥ በሁለት ድርጅቶች መካከል ስምምነት ተፈረመ።

የዕቃ አስተላላፊዎችና መርከብ ወኪሎች ማህበር የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና የሎጂስቲክስ ዘርፍ የአቅም ግንባታ ስራዎችን ለማካሄድ ትሬድ ማርክ ኢስት አፍሪካ ከተሰኘ ድርጅት ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።

ኢትዮጵያ የገቢና ወጪ ንግዱን ለማሳለጥ በድሬዳዋ የከፈተችው ነጻ የንግድ ቀጣና በብቁ የሰው ኃይል እንዲመራና ቀልጣፋ የሎጂስቲክስ አገልግሎት እንዲኖረው እየተሰራ ይገኛል።    

ዛሬ የተፈረመው ስምምነትም በዘርፉ በስልጠና የዳበረ አቅም ለመፍጠር ትልቅ ድርሻ እንዳለው የማህበሩ ፕሬዝዳንት ኤልሳቤት ጌታሁን ተናግረዋል።    

በተለይም በሎጀስቲክስ ዙሪያ የተካሄዱ ዓለም አቀፍ ጥናቶች ለኢትዮጵያ በሚጠቅም መልኩ ለመቀመርና ተሞክሮውን ለማጋራትም የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።     

ማህበሩ በኢትዮጵያ በሎጀስቲክስ ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመለየት የሚረዱ የጥናት ስራዎችና አውደ ጥናቶች የሚያካሂድ ሲሆን ለዚህም ትሬድማርክ ኢስት አፍሪካ የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣና ላይ ተሳትፎ ላላቸው የግሉ ዘርፍና የመንግስት ባለሙያዎችና አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የትሬድ ማርክ  ተጠባባቂ  ዳይሬክተር  አቶ አብነት  በቀለ በበኩላቸው  ድርጅቱ በአፍሪካ በ12 አገራት ላይ ንግድን በሚያሳልጡ ተግባራት ላይ መሰማራቱን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያም የሎጀስቲክስ ዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ የእውቅትና የክህሎት ክፍተቶችን ለመቅረፍ እንደሚሰራ ነው የጠቀሱት።

ከማህበሩ ጋር የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።          

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም