የሀገርን ዘላቂ ልማትና ህልውናን ለማረጋገጥ ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት አምራችና ውጤታማ ሊሆን ይገባል--አቶ መላኩ አለበል

18

አርባ ምንጭ፤ መስከረም 25ቀን 2015(ኢዜአ) የሀገርን ዘላቂ ልማትና ህልውናን ለማረጋገጥ ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት የሥራ መስክ አምራችና ውጤታማ መሆን አለበት ሲሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል አሳሳቡ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸምን የሚገመግም መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ አዘጋጅቷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል እንዳሉት፣በኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት እንዲረጋገጥ ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት መስክ አምራችና ውጤታማ መሆን ይኖርበታል።

የአገራችን ህልውናና ሉዓላዊነትን ጠብቆ ማቆየት የሚቻለው አንድነትን በማጠናከር፣ በማምረትና ውጤታማ በመሆን እንደሆነ ጠቅሰው፣ ለዚህም አመራሩ ወቅቱን የዋጀ የአመራርነት ሚናውን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

"ታሪካችን፣ ባህል እና እምነታችን የሸፈናቸው በርካታ የድህነት ቀንበሮች አሉ" ያሉት ሚኒስትሩ፣ ከድህነት አዙሪት ለመውጣት ያሉ እንቅፋቶችን አልፎ መውጣት እንደሚገባ ገልጸዋል።

"የፀጥታ አካላት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ውድ ሕይወታቸውን ለመስዋዕት እንዳዘጋጁ ሁሉ እኛም አምራች ወታደር በመሆን የሀገር ልማትና ህልውናን ማረጋገጥ ይጠበቅብናል" ብለዋል።

በአገራችን የተቀዛቀዘውን ኢንዱስትሪ ለማነቃቃት ባለፈው ዓመት የተካሄደ “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ  በርካታ ለውጦች እንዲመዘገቡ ማገዙንም ሚኒስትሩ አስታውሰዋል።

በዚህም በመጠንም ሆነ በዋጋ ከፍ ያለ ሥራ በመሰራቱ ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ከወጪ ንግዱ መገኘቱን ተናግረዋል።

በዓመቱም ከ255 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩንና የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም በ2013 ከነበረበት 46 በመቶ ወደ 52 በመቶ ከፍ ለማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

"በተያዘው በጀት ዓመት የዓመቱን ዕቅድ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም በኮሮና ቫይረስ፣ በጦርነት፣ በአገራዊና ዓለም አቀፋዊ ችግሮች ምክንያት ያልተሳኩ ዕቅዶችን ደምረን የተሻለ ውጤት ለማምጣት የምንሰራበት ነው" ሲሉም ሚኒስትሩ አክለዋል።

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው፣ የጋሞ ዞን ከሚታወቅበት ሰላም፣ አብሮነትና መቻቻል ባለፈ ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚሆን በርካታ ሀብቶች እንዳሉት ገልጸዋል።

ለእዚህም በዞኑ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የተለያዩ ማዕድናት፣ የጥጥ ልማት፣ የእንስሳትና እንስሳት ተዋጽኦ በከፍተኛ መጠን መኖሩን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመሆን በዞኑ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ሀብቶችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ስለሚቻልበት ሁኔታ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው መድረክ ከ1ኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ግምገማ በተጨማሪ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የአቅም ግንባታ ስልጠና እንዲሁም የኮሪያ የዕድገት ተሞክሮ ለተሳታፊዎች እንደሚቀርብ ለማወቅ ተችሏል።

በመድረኩ ላይ የሚኒስቴሩ የሥራ አመራሮች፣ የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሥራ ሃላፊዎች፣ ተጠሪ ተቋማት፣ የዘርፍ ማህበራትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም