ቀጥታ፡

በዜጎች ላይ የተፈጸመው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት አሳዛኝና የሚወገዝ ተግባር ነው-የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ኮንግረስ

አዲስ አበባ መስከረም 11/2011 በቡራዩና አካባቢው በዜጎች ላይ የተፈጸመው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት አሳዛኝና የሚወገዝ ተግባር መሆኑን የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ኮንግረስ አስታወቀ። ኮንግረሱ የዜጎችን አንድነትና አብሮነት  ሊያጠናክሩ በሚችሉ እሴቶች ላይ በስፋት መሰራት እንደሚያስፈልግም ጠቁሟል። የኮንግረሱ ሰብሳቢ አቶ ገረሱ ገሳ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዜጎችን ከመኖሪያ ቀዬያቸው የማፈናቀልና ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን መፈጸም በስፋት እየተስተዋለ መጥቷል። በእንደዚህ ዓይነቱ ድርጊት የሚሳተፉት ላይ ተገቢው እርምጃ ባለመወሰዱ ችግሩ መቀጠሉንም ጠቁመዋል። አቶ ገረሱ በቅርቡ በቡራዩና አካባቢው በዜጎች ላይ የተፈጸመው ኢሰባዓዊ ድርጊት አሳዛኝና የሚወገዝ ተግባር መሆኑን ነው የገለጹት። ''በኦሮሞ ወጣቶች ስም በግልጽም ሆነ በህቡዕ ተደራጅቶ ለጥፋት እየተንቀሳቀሰ ያለውን ኃይል መንግሥት አጣርቶ በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲያቀርብም እንጠይቃለን'' ሲሉም ተናግረዋል። በቡራዩና አካባቢው የተፈጸመውን ድርጊት ለመቃወም በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የዜጎች ህይወት መጥፋቱን አስታውሰው፤ መንስኤው በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ መሆን እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል። በቀጣይ መሰል ኢሰብዓዊ ተግባራትን በዘላቂነት ለመፍታት የዜጎችን አንድነት የሚያጠናክሩ እሴቶች ላይ በትኩረት መስራት አስፈላጊ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተውታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም