ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቡና ወደ ውጭ አገራት የሚላክበትን መነሻ ዋጋ ለመወሰን እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ መስከረም 11/2011 የኢትዮጵያ ቡና ወደ ውጭ አገራት የሚላክበትን መነሻ ዋጋ ለመወሰን እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳኒ ረዲ ለኢዜአ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ የቡና ገበያ በርካሽና በተለዋዋጭ ዋጋ ነው እየተሸጠ ያለው። ይኸውም አገሪቱ ከቡናው ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ገቢ እንዳታገኝ ካዳረጉት ምክንያቶች አንዱ ነው ብለዋል። እንደ አቶ ሳኒ ገለጻ ብዙ  የግብርና ምርቶች ወደ ውጭ የሚልኩ አገራት ዝቅተኛ የመላኪያ ዋጋ የሚወስኑ ሲሆን በኢትዮጵያ ግን ይህ አሰራር ስራ ላይ አልዋለም። በመሆኑም የመንግስትና የግሉ ሴክተር በጋራ በመሆን በየጊዜው የዓለም ገበያ ሁኔታን በማጥናት የቡና መነሻ ዋጋ የሚወስኑበት ስርዓት አስፈላጊ ነው ብለዋል። ባለስልጣኑ የቡና የመላኪያ መነሻ ዋጋ ለመወሰን ከንግድ ሚንስቴር ጋር በመቀናጀት በጋራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። አዲሱ የቡና ምርት ወቅት የሚጀምርበት ታህሳስ ወር  ባለው ግዜ ውስጥ የህግ ማዕቀፉ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ ይሆናል ብለን ነው እየሰራን ያለነው ብለዋል። አቶ ሳኒ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ቡና አምራቾች ሕብረት አባል ለመሆን እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ይኸውም የቡና አምራች አገራት በዓለም የቡና ገበያ ዋጋን የመደራደርና የመወሰን አቅም ለማሳደግ እንደሚረዳቸው በማውሳት። የአገሪቱ ቡና በዓለም አቀፍ የቡና ገበያ የሚፈለገውን ጥራት ያሟላ በመሆኑ የቡና አቅርቦቱን ለማሻሻልም ጥራትን የሚያጓድሉ አሰራሮችን የማስወገድና የምርት ዱካውን የጠበቀ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል። በአገሪቱ ቡና ላይ ብቻ ምርምር የሚያደርግ፣ በየስነ ምህዳሩ ተስማሚ የሆኑ ዝርያዎችን የማውጣት፣ የማባዛትና ተደራሽ የማድረግ፤ እንዲሁም  በሽታዎችና ተባይ መከላከል ላይ የሚሰራ እራሱን የቻለ ተቋም አለመኖሩንም ጠቅሰዋል። ይህን መሰል ተቋም ማቋቋም  ታዲያ የአገሪቱ ቡና ጥራትና ምርታማነት ላይ የሚፈለገውን ውጤት ለማግኘት ወሳኝ መሆኑን ነው የገለጹት። የምርምር ተቋሙን ለማደራጀት የሚያስፈልገው ደንብና አደረጃጃት የተዘጋጀ ሲሆን በቅርቡ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት። በሌላ በኩል የቡና አምራቾች በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች  የፀጥታ ችግሮችና አለመረጋጋት በሚከሰቱበት ወቅት በምርታቸው ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል የሚያስችል የህግ ሽፋንና ጥበቃ ያለመኖር በተደጋጋሚ የሚነሳ ችግር መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። የቡና አምራቾች ቡና ከሚያለሙባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ ነዋሪዎችና የአስተዳደር አካላት ጋር ተሳስረው እንዲሰሩና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለመፍጠር የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ መዘጋጀቱንና በቅርቡ ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም አክለዋል። በቡና ዘርፍ ላይ የሚሰሩ ባለ ድርሻ አካላት በርካታ በመሆናቸው ሳቢያም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች ቀልጣፋ አገልግሎት ያለማግኘት ችግር በተደጋጋሚ  እንደሚገጥማቸው የሚነሳ ቅሬታ መሆኑን አንስተዋል። በመሆኑም በዘርፉ የአንድ መስኮት አገልግሎት የመጀመር እቅድ መኖሩን ጠቁመው በጊዜያዊነት ባለስልጣኑ የሌሎች ተቋማትን ስራዎች የማስተባበር ስራ መጀመሩን ነው የገለጹት። የቡና አምራቾች የግብይትና የሽያጭ አቅማቸው ደካማ በመሆኑም የተሻለ ዋጋ የሚከፍሉ ገበያዎችን የማግኘት እድላቸውን አነስተኛ ነው ሲሉም ተናግረዋል። ይህንን ችግር ለመፍታትም ባለስልጣኑ ከአገሪቱ ቡና የሚላክባቸውን አገራት የገበያ አድማስ ለማስፋት እየሰራ ነው ያሉት። በ2010 በጀት አመት 238 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ ተልኮ  862 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን  በተያዘው በጀት አመት 300 ሺህ 420 ቶን ቡና በመላክ 1 ነጥብ 116 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም