ቀጥታ፡

''ኢትዮጵያ የበርካታ ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶች ባለቤት በመሆኗ ከአፍሪካ ቀዳሚና ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ያደርጋታል''-የውጭ ጎብኚዎች

መስከረም 24 ቀን 2015 (ኢዜአ)''ኢትዮጵያ የበርካታ ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶች ባለቤት በመሆኗ ከአፍሪካ ቀዳሚና ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ያደርጋታል'' ሲሉ ከጀርመን የመጡ ጎብኚዎች ተናገሩ፡፡

ከጀርመን በቡድን የመጡ ጎብኚዎች በአለም ቅርስነት የተመዘገበውን የአጼ ፋሲል ቤተ-መንግስትን ዛሬ ጎብኝተዋል፡፡

በጀርመን የአስጎብኚ ድርጅት ባለቤት የሆኑት ዲተር ፎረስን እንዳሉት በኢትዮጵያ የሚገኙ አስደናቂ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ቅርሶች የጎብኚዎችን ቀልብ በመሳብ ረገድ ከአፍሪካ ቀዳሚ ናቸው፡፡

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን የኢትዮጵያውያን ድንቅ የእጅ ጥበብ ሙያ አጉልቶ የሚያሳይ ሰው ሰራሽ ቅርስ መሆኑን ጠቅሰው፤ይህም በጀርመን ዜጎች እጅግ ታዋቂ መሆኑን ገልፀዋል።

በአለም ቅርስነት የተመዘገቡ ቅርሶቿ የውጪ ሀገር ጎብዎችን በመሳብ በኩል የጎላ ፋይዳ አላቸውም ብለዋል፡፡

ከጎብኚዎቹ መካከል ኢዱአርድ ዘሄቱር በበኩላቸው ''ኢትዮጵያ ጥንታዊና የበርካታ ታሪክ ባለቤት መሆኗ ከአፍሪካ ቀዳሚ ቦታ የሚያሰጣት ሀገር ነች'' ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የበርካታ ብዝሃ ባህልና እምነት መገኛ ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፤ ዜጎቿም በአንድነትና በመከባበር አብሮ የመኖር እሴቶችን የገነቡ መሆናቸው ልዩ ያደርጋቸዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

''ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ የመጀመሪያዬ ባይሆንም ሁሌም ስመጣ የህዝቦቿ የእንግዳ ተቀባይነት ባሕልና አክብሮት እጅግ ያስደስተኛል'' ሲሉ ተናግረዋል፡፡

''የቱባ ባህል ባለቤት የበርካታ ቋንቋ ተናጋሪዎችና እምነት ተከታይ ህዝቦች በሰላምና በአብሮነት የሚኖሩባት ታሪካዊ ሀገር ነች'' ያሉት ደግሞ የቡድኑ አባል ፋንክሊ ፋንስ ናቸው፡፡

ጀርመን ሀገር የአስጎብኝ ድርጅት እንደሚመሩ ተናግረው፤ኢትዮጵያ ያላትን የቱሪዝም ሀብት ለጀርመን ህዝብ በማስተዋወቅ መጥተው እንዲጎበኙ ጥረት እንደሚያደርጉም ተናግረዋል፡፡

የጎንደር ከተማ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ ቻላቸው ዳኜ በበኩላቸው የጀርመን ጎብኚዎች ወደ ከተማዋ መምጣት የከተማውን የቱሪዝም ሀብት ለማስተዋወቅ ምቹ አጋጣሚ ነው፡፡

እንዲሁም አካባቢው ለጎብኝዎችም ሆነ ለልማት ሰላማዊ መሆኑን በተጨባጭ ለማሳየት እንደሚያግዝ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም