ቀጥታ፡

በአሜሪካ የአጋማሽ ዘመንምርጫ ለ16 እጩዎች ይሁንታ መስጠቱን የአሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ አስታወቀ

መስከረም 24/2015/ኢዜአ/ በአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ለ16 እጩዎች ይሁንታ (ኢንዶርስመንት) መስጠቱን የአሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ (ኤፓክ) የተባለው ተቋም አስታወቀ።

23ኛው የአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ (ሚድ ተርም ኢሌክሽን) ጥቅምት 29 ቀን 2015 ዓ.ም ይካሄዳል።

ለአሜሪካ ህግ አውጪ ምክር ቤት (ኮንግረስ) 435 መቀመጫዎችና ከአስፈጻሚው (ከሴኔቱ) 100 መቀመጫዎች ውስጥ 34ቱ (አንድ ሶስተኛው) ለምርጫ ይቀርባሉ።

የአሜሪካ ኢትዮጵያውያን የህዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀመንበር በመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ብሔራዊ ቅስቀሳ በይፋ ማስጀመሩ የሚታወስ ነው።

ኮሚቴው በአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ዋነኛ ሚናው ለኢትዮጵያ ጥቅም ይሟገታሉ የሚባሉ እጩዎችን ማስመረጥ እንደሆነ የኮሚቴው ሊቀመንበር መስፍን ተገኑ ለኢዜአ ገልጸዋል።   

እጩዎቹ የኢትዮጵያን እና የአሜሪካንን ታሪካዊ ግንኙነት እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ላይ ትብብር የጋራ ጥቅምንና መርህን ባስጠበቀ መልኩ የማስቀጥል ስራ ያከናውናሉ ተብለው እምነት እንደተጣለባቸው ተናግረዋል።

እጩዎቹ የኢትዮጵያን ወዳጆች ያካተተና ዳያስፖራው የተስማማባቸው እንደሆነ አመልክተዋል።

ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት ኮሚቴው (ኤፓክ)16 እጩዎች (ኮንግረስና ሴኔት) ይሁንታ (ኢንዶርስመንት) መሰጠቱንና አብዛኞቹ የኮንግረስ አባል መሆናቸውን አመልክተዋል።

ከእጩዎቹ መካከል ቶማስ ኪን ጁኒየር (ኒው ጀርዚ ሪፐብሊካን ፓርቲ) እና ሲድኒ ካምላገር (ካሊፎርኒያ ዴሞክራቲክ ፓርቲ) የኮንግረስ አባል ለመሆን ከሚወዳደሩት እጩዎች መካከል ይገኙበታል።

እጩዎቹ ቢመረጡ በአሜሪካ ሕግ አውጪ ምክር ቤቶች የተዳከመውን የኢትዮጵያ ደጋፊ ስብስብን (ኮከስ) እንደሚያጠናክሩ ነው አቶ መስፍን ያስረዱት።

ከ16 እጩዎች ውጪ በቅርቡ ተጨማሪ ስድስት እውቅና የተሰጣቸው እጩዎች ይፋ እንደሚሆኑም ጠቁመዋል።

ኮሚቴው በአሜሪካ በሚገኙ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ጋር በጋራ የተቋቋሙ የሲቪክ ተቋማትና የዳያስፖራ አደረጃጀቶች ጋር በመቀናጀት ለምርጫው የዝግጅት ስራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በአሜሪካ ከሚገኙ 50 ግዛቶች ትውልደ-ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች በብዛት የሚገኙባቸውን ቦታዎች ታሳቢ በማድረግ በ22ቱ ግዛቶች ብሔራዊ የምርጫ ኮሚቴዎችን አቋቁሞ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ትውልደ-ኢትዮጵያውኑ በርከት ብለው በሚሰበሰቡባቸው አካባቢዎች የመመዝገብና ድምጽ እንዲሰጡ ቅስቅሳ እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ቨርጂኒያ፣ ጆርጂያ፣ ፔንሲልቫኒያና ካሊፎርኒያ ግዛቶችን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ድምጽ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የተመረጡት ግዛቶች ከዚህ ቀደም በነበሩ ምርጫዎች እጩዎች በተወሰኑ ድምጾች የሚለያዩባቸው በመሆኑ ዳያስፖራው ልዩነት መፍጠር እንደሚችል ነው አቶ መስፍን ያብራሩት።

ዳያስፖራው እውቅና ያገኙ እጩዎች ቅስቀሳ በመሳተፍና የምርጫ ቀን በነቂስ በመውጣት መብቱን ተጠቅሞ ለኢትዮጵያ ጥቅም መጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ኮሚቴው (ኤፓክ) እ.አ.አ በ2024 በሚካሄደው የአሜሪካ አጋማሽ ዘመን ምርጫ በተመሳሳይ በኮንግረስና በሴኔት ኢትዮጵያን የሚደግፉ ተመራጮች ውክልና ወደ 10 በመቶ ለማሳደግ እቅድ መያዙን አቶ መስፍን ጠቁመዋል።

ኮሚቴው በቀጣይ በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቁ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆችን ተሳትፎ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ አክለዋል።

በምክር ቤት (ኮንግረስ) ምርጫ የሚያሸንፍ እጩ ለሁለት ዓመት እንዲሁም የሴኔት ተወዳዳሪ ለስድስት ዓመት ይቆያል።

እ.አ.አ በ2021 የቨርጂኒያ ገዢ ምርጫ በትውልደ-ኢትዮጵያውያን አና በኢትዮጵያ ወዳጆች ድምጽ ታግዘው የሪፐብሊካን ፓርቲ እጩው ግሌን ያንግኪን የዴሞክራቲክ ፓርቲ እጩን ቴሪ ማካውሊፍን አሸንፈው የግዛት ገዢ ሆነው መመረጣቸው የሚታወስ ነው።

የኮንግረሱ አባል እጩዎቹም ሼይላ ጃክሰን ሊ (ኒው ዮርክ ዴሞክራቲክ ፓርቲ)፣ ብራያን ፊትዝፓትሪክ (ፔንሲልቫኒያ ሪፐብሊካን ፓርቲ)፣ ጆን ጋራሜንዲ (ካሊፎርኒያ ዴሞክራቲክ ፓርቲ)፣ አል ግሪን (ቴክሳስ ዴሞክራቲክ ፓርቲ)፣ ስቴቨን ሆርስፎርድ (ኔቫዳ ዴሞክራቲክ ፓርቲ)፤ ትሬንት ኬሊ (ሚሲሲፒ ሪፐብሊካን ፓርቲ)፣ ጂሚ ፓኔታ (ካሊፎርኒያ ዴሞክራቲክ ፓርቲ)፣ ጋይ ሬስቼንትሀለር (ፔንሲልቫኒያ ሪፐብሊካን ፓርቲ)፣ ዴቪድ ሽዋይከርት (አሪዞና ሪፐብሊካን ፓርቲ) እና ክሪስ ስሚዝ (ኒው ጀርዚ ሪፐብሊካን ፓርቲ) ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም