የኢትዮጵያ በርካታ እሴቶች እና ታሪካዊ ኩነቶች በብዙ መልኩ የተሳሰሩና ለአገራዊ አንድነት መጠናከር ወሳኝ ናቸው-ኤምሬተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ በርካታ እሴቶች እና ታሪካዊ ኩነቶች በብዙ መልኩ የተሳሰሩና ለአገራዊ አንድነት መጠናከር ወሳኝ ናቸው-ኤምሬተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ
መስከረም 24/2015 /ኢዜአ/ የኢትዮጵያ በርካታ እሴቶች እና ታሪካዊ ኩነቶች በብዙ መልኩ የተሳሰሩና ለአገራዊ አንድነት መጠናከር ወሳኝ መሆናቸውን የታሪክ ኤምሬተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማህበር "ትስስርና መስተጋብር በኢትዮጵያ ታሪክ" በሚል መሪ ሀሳብ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ በተዘጋጀ መድረክ ውይይት ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የታሪክ ኤምሬተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፤ በኢትዮጵያ የታሪክ ምልከታዎችን በማዛባትና በማደናገር ከአብሮነትና ትብብር ይልቅ ልዩነት እንዲጎላ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ደግሞ ለአገርም ይሁን ለትውልድ የማይበጅ መሆኑን ጠቅሰው፤ በጉዳዩ ዙሪያ እውነተኛውን ነገር የሚያሳዩ የተሰሩ ጥናቶች እየቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ በርካታ እሴቶች እና ታሪካዊ ኩነቶች በብዙ መልኩ የተሳሰሩና ለሌሎች አገሮችም ጭምር መሰረት ያኖሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በተለይም ወጣቶች ስለታሪክ ያላቸውን ብዥታ ለማጥራት ትክክለኛውን መረጃ መረዳትና የተሳሳተ ትርክት ሰለባ ሊሆኑ አይገባም ብለዋል።
ለዚህም ከረዥም ዓመታት በኋላም ቢሆን የታሪክ ትምህርት ለመጀመር የማስተማሪያ መጽሐፍ /ሞጁል/ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
የመጀመሪያ ረቂቅ ከታሪክ ትምህርት ክፍሎች በተገኘ ግብዓት ዳብሮ አጨቃጫቂ የሆነ ክፍልም በሚያስማሙ ሁኔታ መስተካከሉን ተናግረዋል።
የታሪክ ማስተማሪያ መጽሐፍቱ መዘጋጀቱን ጠቅሰው፤ በዚህ ዓመት ትምህርት ለመጀመር ለትምህርት ሚኒስቴር ምክረ-ሀሳብ ማቅረቡን ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይ ጥናታዊ ጽሑፎች ካቀረቡት ምሁራን መካከል ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ያሉ የሕዝቦች ትስስርና መስተጋብሮች ለኢትዮጵያ አንድነት መሰረት መሆናቸውን አስረድተዋል።
የቋንቋ አካታችነት ለአገር ግንባታ ለእርስ በርስ መቀራረብ፣ አብሮነት፣ ለመተሳሰብና ብዝሃነትን ለማጠናከር እንዲሁም ለአገራዊ አንድነትና ሰላም ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።
የብዝሃነት ጥያቄ ሳይንሳዊ፣ እውቀትን መሰረት ባደረገ እና በባለሙያ ቢተገበር ውጤታማ እንደሚሆንም አመላክተዋል።
በገበያ ሥፍራዎችና ሌሎችም ማህበራዊ ተቋማት መስተጋብሮች፣ የቋንቋና የባህል ውርርስ በማድረግ ኢትዮጵያዊ አብሮነትን ማጠናከር እንደሚቻል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ግርማ ነጋሽ አስረድተዋል።