ቀጥታ፡

የሳይንስ ሙዚየም መገንባቱ ለህጻናትና ወጣቶች የፈጠራ ሃሳብ ልምምድና የፈጠራ እድገት የላቀ ሚና ይኖረዋል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ

መስከረም 24/2015 /ኢዜአ/ በኢትዮጵያ የሳይንስ ሙዚየም እውን መሆኑ ለህጻናትና ወጣቶች የፈጠራ ሃሳብ ልምምድና የፈጠራ እድገት የላቀ ሚና ይኖረዋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።

የሳይንስ ሙዚየም የተሻለች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በልጆች ላይ መሰረት የሚጥል ነውም ብለዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በመሃል አዲስ አበባ የተገነባውን የሳይንስ ሙዚየም መርቀው ከፍተዋል።

የሳይንስ ሙዚየም የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ምኞት መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሌሎች አገሮች የሳይንስ ሙዚየም በተመለከቱበት አጋጣሚ በኢትዮጵያ እውን ለማድረግ ጉጉትና ቁጭት እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል።

አሁን ላይ ህልም የነበረው ጉዳይ እውን ሆኖ ሁለገብና አስደናቂ የሳይንስ ሙዚየምን በአዲስ አበባ መገንባቱን ገልጸዋል።

የሳይንስ ሙዚየም በተለይም የታዳጊና ህጻናት ልጆች የሳይንስና የፈጠራ ህልም እውን የሚሆንበት ስለመሆኑ ተናግረዋል።

በቴሌቪዥን ህፃናት ሲመለከቷቸው የነበሩ የተለያዩ የሳይንስ መገለጫዎችን በሙዚየሙ በአካል የመመልከት እድል ማግኘታቸው ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።

የሳይንስ ሙዚየም ህጻናትና ወጣቶች የፈጠራ ሀሳቦችን እንዲለማመዱና እንዲያሳድጉ የሚያስችሉ ማዕከላት እንዳሉት ጠቅሰው ይህም የተሻለች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ለሚደረገው ጥረት መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።

በሙዚየሙ በዛሬው እለት የተከፈተው ኤግዚቪሽን ለሚቀጥሉት 20 ቀናት ለህዝብ ዕይታ ክፍት መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ወላጆችና ትምህርት ቤቶች ጭምር ህጻናትን ወደ ሙዚየሙ በማምጣት እንዲያስጎበኙ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች የህጻናትና የወጣቶችን የፈጠራ ሙከራ በመደገፍ ለሀገራቸውና ለትውልዱ አለኝታ እንዲሆኑም ጠይቀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው፤ የሳይንስ ሙዚየሙ ኢትዮጵያን በዘመናዊው ዓለም ተወዳዳሪ የሚያደርግ አስደናቂ ስራ መሆኑን ገልጸዋል።

በሳይንስና ቴክኖሎጂ የላቀች ሀገር ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት ህፃናትና ወጣቶች የጎላ ሚና እንዲኖራቸው የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤም፤ የሙዚየሙ መገንባት ለከተማዋ ውበትን እንዲሁም ለትምህርት ተቋማትና አጠቃላይ ወጣቶች እውቀትን የሚያጎናጽፍ መሆኑን ተናገረዋል።

አዲስ አበባን በሁሉም ዘርፍ ተመራጭ ወይም “ስማርት ሲቲ“ ለማድረግ የተጀመረውን እቅድ እውን ለማድረግም የላቀ ፋይዳ ይኖረዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም