ተቋማቱ የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና የሎጂስቲክስ ዘርፍ አቅምን ለማሳደግና አሰራሩን ለማሳለጥ ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
ተቋማቱ የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና የሎጂስቲክስ ዘርፍ አቅምን ለማሳደግና አሰራሩን ለማሳለጥ ተስማሙ
መስከረም 24/2015 (ኢዜአ) የዕቃ አስተላላፊዎችና መርከብ ወኪሎች ማህበር የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና የሎጂስቲክስ ዘርፍ የአቅም ግንባታ ስራዎችን ለማካሄድ ትሬድ ማርክ ኢስት አፍሪካ ከተሰኘ ድርጅት ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።
ኢትዮጵያ የገቢና ወጪ ንግዱን ለማሳለጥ በድሬዳዋ የከፈተችው ነጻ የንግድ ቀጣና በብቁ የሰው ኃይል እንዲመራና ቀልጣፋ የሎጂስቲክስ አገልግሎት እንዲኖረው እየተሰራ ይገኛል።
ዛሬ የተፈረመው ስምምነትም በዘርፉ በስልጠና የዳበረ አቅም ለመፍጠር ትልቅ ድርሻ እንዳለው የማህበሩ ፕሬዝዳንት ኤልሳቤት ጌታሁን ተናግረዋል።
በተለይም በሎጂስቲክስ ዙሪያ የተካሄዱ ዓለም አቀፍ ጥናቶች ለኢትዮጵያ በሚጠቅም መልኩ ለመቀመርና ተሞክሮውን ለማጋራትም የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።
ማህበሩ በኢትዮጵያ በሎጂስቲክስ ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመለየት የሚረዱ የጥናት ስራዎችና አውደ ጥናቶች የሚያካሂድ ሲሆን ለዚህም ትሬድማርክ ኢስትአፍሪካ የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
በድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣና ላይ ተሳትፎ ያላቸው የግሉ ዘርፍና የመንግስት ባለሙያዎችና አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የትሬድማርክ ኢስት አፍሪካ ተጠባበቂ ዳይሬክተር አቶ አብነት በቀለ በበኩላቸው ድርጅቱ በአፍሪካ በ12 አገራት ላይ ንግድን በሚያሳልጡ ተግባራት ላይ መሰማራቱን ጠቅሰዋል ።
በኢትዮጵያም የሎጂስቲክስ ዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ የእውቅትና የክህሎት ክፍተቶችን ለመቅረፍ እንደሚሰራ ነው የጠቀሱት።
ከማህበሩ ጋር የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።