የአፍሪካን ቀጣናዊ የንግድ ትስስር ለማሳለጥ በሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያውያን ባለ ሃብቶች ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል- የኢትዮጵያ የቀድሞ መሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካን ቀጣናዊ የንግድ ትስስር ለማሳለጥ በሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያውያን ባለ ሃብቶች ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል- የኢትዮጵያ የቀድሞ መሪዎች
መስከረም 24/2015 /ኢዜአ/ የአፍሪካን ቀጣናዊ የንግድ ትስስር ለማሳለጥ በሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያውያን ባለ ሃብቶች ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ የቀድሞ መሪዎች ገለጹ።
በኢትዮጵያና በኢጋድ ቀጠና ሠላምና ልማት ላይ የሚሰራው ኢንትፕረነሪያል ፎረም ፎር ፒስ ኤንድ ዴቨሎፕመንት የተሰኘው ተቋም በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ቢውለደር ሽልማት አሸናፊ ለሆኑት ኢትዮጵያዊው ባለሀብት አይሸሽም ተካ የምስጋና መርሃ-ግብር አከናውኗል።
በመርሀ ግብሩ ላይ የኢንተርፕርነር ፎረም ፎር ፒስ ኤንድ ደቨሎፕመንት የስራ አስፈፃሚ ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እና የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ እንዲሁም የተለያዩ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።
የተቋሙ መስራች አባል የሆኑት ኢትዮጵያዊው ባለሀብት አይሸሽም ተካ፤ በምጣኔ ሃብት ዕድገት ባስመዘገቡት የላቀ ውጤት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ቢውለደር ሽልማት ማሸነፋቸውን ተከትሎ ድርጅቱ የምስጋና መርሃ-ግብር አዘጋጅቶላቸዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት መልዕከት ያስተላለፉት የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ፤ በኢትዮጵያና በኢጋድ ቀጣና ሰላምና ልማት ላይ ተቋሙ የሚሰራ መሆኑን ጠቅሰው ባለሀብቱ የዚህ ተቋም መስራች አባል መሆናቸውን ተናግረዋል።
በስራ ፈጣሪዎች የተመሰረተ ተቋም መሆኑን የሚያመላክት እና በቀጣይ ድርጅቱ ለሚሰራቸው ስራዎች ጉልበትና አቅም የሚፈጥር ሽልማት መሆኑንም ነው የተናገሩት።
የቀድሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ በበኩላቸው ባለሀብቱ ኢትዮጵያና ጎረቤት ሀገራትን በቢዝነስና ዲፕሎማሲ ግንኙነት በማስተሳሰር ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በምጣኔ ሃብት ዕድገት ባስመዘገቡት የላቀ ውጤት የተሸለሙት አቶ አይሸሽም ከታች ተነስተው ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ የቻሉና ታላቅ ምሳሌ የሚሆኑ ባለሃብት መሆናቸውን ገልጸዋል።
የአፍሪካን ቀጣናዊ የንግድ ትስስር ለማሳለጥ በሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያውያን ባለ ሃብቶች ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
በሽልማት ስነ ስርዓቱ በተጓዳኝ ከበርካታ ሀገራት ባለሀብቶች ጋር ለሀገር በሚጠቅሙ በርካታ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት መደረጉን አቶ አይሸሸም ገልጸዋል።
ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ከቀጣናው ባለፈ ከሌሎች የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ጋር በንግድ ለማስተሳሰር ትልቅ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
በተደረገላቸው የምስጋና መርሀ-ግብር መደሰታቸውን ገልጸው በቀጣይ ለኢትዮጵያ ብሎም ለቀጣናዊ ሰላም፣ ልማትና የንግድ ትስስር አበክረው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
አቶ አይሸሽም ተካ በቀን ሰራተኝነት 7 ብር ደሞዝ ተቀጥረው ስራን ሳይንቁ በመስራት አሁን ላይ ባለሀብት መሆን ችለዋል።
በምጣኔ ሃብት ዕድገት የላቀ ውጤት የተሸለሙት አቶ አይሸሽም ተካ፤ ላለፉት 15 ዓመታት ኑሯቸውን በደቡብ ሱዳን ጁባ አድርገው የተለያዩ የንግድ ስራዎችን በማከናወን ይታወቃሉ።
በደቡብ ሱዳን ቆይታቸው በሰላም፣ ልማትና ሰብዓዊ ድጋፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እኤአ በ2019 ከደቡብ ሱዳን መንግስት የክብር ዜግነት ተሰጥቷቸዋል።
አንተርፕረነሪያል ፎረም ፎር ፒስ ኤንድ ደቨሎፕመንት (EFPD) መስከረም 25 ቀን 2014 ዓ.ም. በዶክተር ሙላቱ ተሾመ እና አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ተቋቁሞ በኢጋድ ቀጣና ላይ ሰላም እና ልማትን ለማጎልበት እየሰራ ያለ ድርጅት ነው፡