በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል 18 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ ስንዴን በመስኖ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል 18 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ ስንዴን በመስኖ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው
ሚዛን አማን፣ መስከረም 24 ቀን 2015 (ኢዜአ)፡- በክልሉ በዘንድሮ የበጋ ወቅት 18 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ ስንዴን መስኖ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ ውስጥ በሚገኙ ሁሉም ዞኖች ውስጥ ያለው የመስኖ መስመርና ወንዞች የመለየት ስራ ከዝግጅቱ መካከል እንደሚገኝበት የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ አሸናፊ ክንፉ ገልጸዋል።
ይህም ስራ የስንዴ ለማልማትን ውጤታማ ለማድረግ መሆኑን አመልክተው፤ ከሚለማው 18 ሺህ ሄክታር የስንዴ ማሳ 900 ሺህ ኩንታል የስንዴ ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
ሥራው በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እና የመንግስት ዋና ተጠሪ እንደሚመራ የጠቀሱት አቶ አሸናፊ፤ በክልል ደረጃ የቴክኒክ ኮሚቴ ተዋቅሮ የንቅናቄ ሥራ መጀመሩን ጠቁመዋል።
"በቀጣይም እስከ ቀበሌ ድረስ የቴክኒክ ኮሚቴ በማዋቀር የስንዴ ልማት ሥራን የተሳካ ለማድረግ በትኩረት ይሰራል" ብለዋል።
ከ30 አስከ 100 ሄክታር ማልማት የሚችሉ 82 ዘመናዊ የመስኖ ተቋማት መለየታቸውን ጠቁመው፤ የመስኖ መስመር ዝርጋት ላይ እንደ ክልል ያለውን ውስንነት ችግር ለማቃለል ግንዛቤ የማሳደግና የቴክኖሎጂ አቅርቦት ላይ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ አምና በሙከራ ደረጃ 432 ሄክታር ላይ ከለማው ማሳ ከ13 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን የቢሮው ምክትል ሃላፊው አውስተዋል።
ተግባሩ አዲስ እንደመሆኑ በቀጣይ አጠናክሮ ለማስቀጠል የተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት እንዲደግፉ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ለ300 ሄክታር ማሳ የሚሆን የዘርና አፈር ማዳበሪያ ድጋፍ መገኘቱን አመላክተዋል።
በክልሉ የቤንች ሸኮ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ሃላፊ አቶ አሥራት ኬዳ፤ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ውጤታማ እንደሚያደርግ ከአምናው የሙከራ አፈጻጸም ተሞክሮ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
በምርት ዘመኑ ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ላይ የበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተው፤ አካባቢው ለዘርፉ ያለውን አመቺነት በመጠቀም ልማቱን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ ከ50 ሄክታር በላይ ማሳ ማልማት የሚችሉ የመስኖ ፓምፖች እንዳሉ ጠቁመዋል።
የስንዴ ልማት በሀገር ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶት ለማስፋፋት ርብርብ እየተደረገ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት "እስካሁን ያስመዘገብነውን የስንዴ ምርታማነት እያጠናከርን እና እያስፋፋን ከሄድን፣በምግብ ራሳችንን ከመቻል አልፈን ለቀጣናችን የዳቦ ቅርጫት መሆን እንችላለን" ብለዋል።
በጀመርነው የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ስንዴን ለውጪ ሀገር ገበያ ለማቅረብ ወደያዝነው ግብ ቀርበናል ሲሉም በመስክ ላይ የሚገኘው የዘርፉን ተስፋ ሰጪ ልማት በማመላከት ገልጸዋል ።