ቀጥታ፡

በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የጉራጌ ዞን ተወላጆች ለዞኑ ልማት በየዓመቱ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ- የዞኑ አስተዳደር

መስከረም 24 ቀን 2015 (ኢዜአ) ከጉራጌ ዞን ውጪ የሚኖሩ የዞኑ ተወላጆች ለአካባቢያቸው ልማት በየዓመቱ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ የዞኑ አስተዳደር ገለጸ።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል፤ የአካባቢው ተወላጆች በተለያዩ የልማት ተግባራትና ማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎችም የዞኑ ማህበረሰብ ሰፊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተሳትፎ በማድረግ ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የዞኑ ተወላጅ የወጣበትን አካባቢ ማህበረሰብ የማይዘነጋ፣ በልማት፣ በሰላምና በማህበራዊ አገልግሎት ተሳትፎ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የዞኑ ተወላጆች በተሰማሩበት መስክ ውጤታማ ለመሆን በታታሪነት የሚሰሩ መሆናቸውን ገልጸው፤ በሚያስመዘግቡት ውጤት የጉራጌ ዞን በመልካም እንዲነሳ የሚያደርጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በሌሎች አካባቢዎችም ተሳትፎ ያለው ተወላጁ የትውልድ አካባቢውን በማልማት ረገድ የጎላ ሚና እንደሚጫወትም ጠቁመዋል።

ዞኑ ያለውን የሰው ሃብትና የመልማት አቅም አሟጦ የመጠቀም ክፍተት እንዳለበት ተናግረዋል።

በመሆኑም ተወላጁ ተሳትፎውን በኢንቨስትመንት እንዲደግም የሚያስችል እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ መሆኑን አመልክተው፤ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ስምሪትና የማስተባበር ተግባር እየተከናወነ እንደሆነ ዋና አስተዳዳሪው ጠቁመዋል።

ወልቂጤ ከተማ በ180 ሚሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ሆቴል አስገንብተው ለአገልግሎት ያበቁት ባለሃብት ዮሐንስ ሃይሌ፤ በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ የዞኑ ተወላጅ ባለሃብቶች በትውልድ አካባቢያቸው እንዲያለሙ ጠይቀዋል።

የዞኑ አስተዳደር ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንዳለበት አስገንዝበው ባለሃብቱ ለመስራት ፍላጎት እንዲኖረው የሚያስችል የአገልግሎትና የመሰረተ ልማት ሁኔታ እንዲሟላ ጥረት መደረግ እንዳለበት ጠቁመዋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም