ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ እያስመዘገበች ያለው ስኬት ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ መሰረት የሚጥል ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ

መስከረም 24 ቀን 2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቴክኖሎጂ ዘርፍ እያስመዘገበች ያለው ስኬት ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ መሰረት የሚጥል ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

ጉባኤው በዋናነት በአፍሪካ የጸጥታና ደህነትን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ላይ አርተፊሻል ኢንተለጀንስን ተግባራዊ ማድረግ በሚቻልበት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ለውጥ እያስመዘገበች መሆኑን አንስተው፣ ዛሬ የተመረቀውን የሳይንስ ሙዚየምን በዚህ ረገድ በአብነት አንስተዋል።

ሙዚየሙ የኢትዮጵያን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እውን በማድረግ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ የነገ አገር ተረካቢ ህፃናት በሳይንስና ፈጠራ ጎልብተው እንዲያድጉ መሰረት የሚጥል መሆኑን ገልፀዋል።

ይህም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ መሰረት የሚጥል መሆኑን ነው የተናገሩት።

በጉባኤው የአገራቸውን ተሞክሮ ያቀረቡት የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የሳይበር ደህንነት ሃላፊ ዶክተር መሃመድ አልኩዌቲ በበኩላቸው አገራቸው ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ትኩረት ሰጥታ በመስራቷ አሁን ላይ በዘርፉ ቀዳሚ ከሆኑ አገራት ተርታ መቀመጧን ተናግረዋል።

ዲጂታል ኢኮኖሚን የመገንባት ሂደት እጅግ ፈታኝ መሆኑን ጠቅሰዉ፤ ቴክኖሎጂን ከማስፋፋት ጎን ለጎን የሳይበር ደህንነት ላይ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

አገራቸው በሳይበር ደህንነት መስክ በርካታ ፈተናዎችን ስለማለፏም አብራርተዋል።ኢትዮጵያ ለዘርፉ የሰጠችውን ትኩረትም አድንቀዋል።

የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢኒጂነር ወርቁ ጋቸና በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ በአፍሪካ በዘርፉ ቀዳሚ የምርምር ተቋም ለመሆን እየሰራ ነው ብለዋል።

ጉባኤውም የዚሁ አካል ስለመሆኑ አንስተዋል።

በአለም አቀፍ ደረጃ እ.አ.አ በ2022 አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም 3 ነጥብ 1 ትሪሊዮን ዶላር የሚያወጣ የቢዝነስ እንቅሰቃሴ ተከናውኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም