ቀጥታ፡

ማህበሩ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት የእህልና የአልባሳት ድጋፍ አደረገ

ጎባ፤መስከረም 24/2015/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የባሌ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በተለያየ ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው ደሎ መና ወረዳ ለተጠለሉ ዜጎች 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት የእህልና የአልባሳት ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ፡፡

በማህበሩ የባሌ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሾመ አባቡ  ድጋፉን  ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት፤ ድጋፉ በተለያዩ ምክንያቶች ከቀያቸው ለተፈናቀሉ 500 ወገኖች የሚሆን ነው ብለዋል።

በአካባቢው በድርቅና ሌሎች ሰው ሰራሽ አደጋዎች  ሳቢያ  ለችግር  የተጋለጡ  ወገኖች ለከፋ ጉዳት እንዳይጋለጡ ለማገዝም የብርድ ልብስ፣ የምግብ ማብሰያ ቁሳቁስ፣ የመጠለያ ሸራና የተለያዩ አይነት የምግብ እህል እንደሚገኙበት አመልክተዋል፡፡

በቀጣይም ድጋፉን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ሀላፊው አስታውቀዋል፡፡

የደሎ መና ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አወል ከድር በበኩላቸው፤  መንግስት  በወረዳው በዝናብ እጥረትና በተለያዩ ምክንያቶች ለድርቅ አደጋ የተጋለጡና ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ለከፋ ጉዳት እንዳይጋለጡ እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በ'ሴፍቲ ኔት' መርሃ-ግብር ከሚደረገው ድጋፍ በተጓዳኝ ለጋሽ ድርጅቶች የሚያደርጉት ድጋፍ ትልቅ አቅም በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመልክቷል፡፡

በወረዳው ከሌ ጎልባ ቀበሌ ከተጠለሉ ተጎጂዎች መካከል አቶ አህመድ ሙስጠፋ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

''አሁን የተደረገልን ድጋፍ የነበረብንን ችግር በተወሰነ መልኩ ያቀልልናል ''ያሉት ሼህ አብደላ'' መንግስትና ሌሎች የልማት ድርጅቶች እንዲደግፉን እንፈልጋለን'' ብለዋል፡፡

የዝናብ እጥረት ባስከተለው ድርቅና ሌሎች ሰው ሰራሽ አደጋዎች በዞኑ ስድስት የአርብቶ አደር ወረዳዎች ጉዳት ማድረሱን  ከኦሮሚያ የቡሳ  ጎኖፋ የባሌ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት  ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም