በአጭር ጊዜ ውስጥ በቴክኖሎጂ ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው ስኬት ለዲጅታል ኢትዮጵያ መሰረት የሚጥል ነው-- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
በአጭር ጊዜ ውስጥ በቴክኖሎጂ ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው ስኬት ለዲጅታል ኢትዮጵያ መሰረት የሚጥል ነው-- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ
መስከረም 24/2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቴክኖሎጂ ዘርፍ እያስመዘገበች ያለው ስኬት ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ መሰረት የሚጥሉ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
ጉባኤው በዋናነት በአፍሪካ የጸጥታና ደህነትን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ላይ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን ተግባራዊ ማድረግ በሚቻልበት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውሰጥ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ለውጥ አያስመዘገበች መሆኑን አስታውቀዋል።
ዛሬ የተመረቀውን የሳይንስ ሙዚየም ለአብነት በመጥቀስ።
ሙዚዬሙ የኢትዮጵያን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እውን በማድረግ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ የነገ አገር ተረካቢ ህፃናት በሳይንስና ፈጠራ ጎልብተው እንዲያድጉ መሰረት የሚጥል መሆኑንም የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ መሰረት የሚጥል መሆኑን ነው የተናገሩት።
በጉባኤው የተባበሩት አረብ ኢምሬትስን የዘርፉ ተሞክሮ ያቀረቡት የአገሪቷ የሳይበር ደህንነት ሃላፊ ዶክተር መሃመድ አልኩዌቲ በበኩላቸው አገራቸው ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ትኩረት ሰጥታ በመስራቷ አሁን ላይ በዘርፉ ቀዳሚ ከሆኑ አገራት ተርታ መቀመጧን ተናግረዋል።
ዲጂታል ኢኮኖሚን የመገንባት ሂደት እጅግ ፈታኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ቴክኖሎጂን ከማስፋፋት ጎን ለጎን የሳይበር ደህንነት ላይ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
አገራቸው በሳይበር ደህንነት መስክ በርካታ ፈተናዎችን ማለፏንም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ለዘርፉ የሰጠችውን ትኩረት አድንቀዋል።
የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ በአፍሪካ በዘርፉ ቀዳሚ የምርምር ተቋም ለመሆን እየሰራ ነው ብለዋል።