የእንስሳት ሃብት ልማትን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ዕቅድና ስትራቴጂ ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
የእንስሳት ሃብት ልማትን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ዕቅድና ስትራቴጂ ተዘጋጀ
መስከረም 24/2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የእንስሳት ሃብት ልማትን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ዕቅድና ስትራቴጂ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍሬ-ዓለም ሽባባው ተናገሩ።
የልማት ዕቅድና ስትራቴጂውን ለማሳካት በዩኒቨርሲቲዎች በእንስሳት ሃብት ልማት ዘርፍ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል።
አገር ዓቀፍ የእንስሳት ባለሙያዎች መር የኅብረት ስራ ማህበራት ልማት ይፍ ማድረጊያ ሥነ ስርዓት በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ኅብረት ስራ ማህበራት ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍሬ-ዓለም ሽባባው፤ በእንስሳት ሃብት ላይ ውጤታማ ስራ ለማከናውን የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
የእንስሳት ሃብት ልማትን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ዕቅድና ስትራቴጂ መዘጋጀቱን ጠቁመው በዩኒቨርሲቲዎች በእንስሳት ሃብት ልማት በሚጀመረው የትምህርት ዘርፍ ምሩቃን እንደሚኖሩ ተናግረዋል።
በቀጣይም ብቁ የሆኑ የእንስሳት ዘርፍ ምሩቅ ሙያተኞችን በማብቃት በምርምር ላይ የተመሰረተ ውጤታማ የእንስሳት ሃብት ልማት እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
በከተሞች እየጨመረ የመጣውን የእንስሳት ተዋጽኦ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት 90 የእንስሳት አልሚ ማኅበራት የሚደራጁ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በሁለቱ ከተማ አስተዳደርና የክልል ከተሞች ማኅበራቱ እንደሚደራጁ ጠቁመው የልማት ባንክ ድጋፍም የማይተካ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በሰብል ልማት ላይ እያካሄደች ያለውን ስኬታማ ተግባር በእንስሳት ሃብት ልማትም ለማሳካት በልዩ ትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ወይዘሮ ፍሬዓለም ገልጸዋል።
በሥነ ስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕረሰዚደንት ዮኃንስ አያሌው ጨምሮ የክልል ግብርና ቢሮ እና የኅብረት ስራ ማህበራት ባለሙያና ኃላፊዎች፣ በእንስሳት ሃብት ንግድ የተሰማሩ ግለሰቦች፣ ሞያተኞችና ሌሎችም ተገኝተዋል።