የቬትናም ፕሬዝዳንት ትራን ዳይ ኩዋንግ በ61 ዓመታቸው አረፉ

104
አዲስ አበባ መስከረም 11/2011 የኤዥያዊቷ ቬትናም ፕሬዝዳንት ትራን ዳይ ኩዋንግ በከባድ ህመም ሲሰቃዩ ቆይተው በ61 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ፕሬዝዳንቱ የአገር ውስጥና የውጭ ዶክተሮች ህክም ቢያደርጉላቸውም ህይወታቸውን ማትረፍ አልቻሉም። በሀገሪቱ ሀኖይ ግዛት በሚገኝ ወታደራዊ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው እያለ ህይወታቸው ማለፉን የአገሪቱን ቴሌቪዥን ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል። ፕሬዘዳንት ትራን ዳይ ኩዋንግ ከፖሊስነት እስከ ፖሊስ ጄነራልነት እንዲሁም የሀገሪቱ የደህንነት መስሪያ ቤት ሚኒስትር በመሆን ለ 40 ዓመታት አገልግለዋል። የኮሚኒስት ፓርቲ መሪ የሆኑት ትራን ዳይ ኩዋንግ እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2016 ነበር የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት። በቬትናም አዲስ ፐሬዝዳንት እስኪመረጥም በጊዜያዊነት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ዳንግ ታይ ንጎክ የመሪነት ቦታውን ይረከባሉ ተብሏል። አዲሱ የቬትናም ፕሬዝዳንት በአገሪቱ የኮሙኒስት ፓርት ማዕከላዊ ኮሚቴ ቀርቦ በጠቅላላ ጉባኤው እንደሚመረጡም ቢቢሲ በዘገባው አስፍሯል። ፕሬዝዳንት ኳንግ ባለፈው ነሀሴ ወር በኢትዮጵያ በነራቸው ጉብኝት ከኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ  እና ከሌሎች የአገሪቱ ባለስልጣናት ጋር በሁለቱ አገሮች መካከል ስላለው ግንኙነት መምከራቸውና ዘርፈ ብዙ ስምምነቶችን መፈራረማቸው ይታወሳል። ኢትዮጵያና ቬትናም በይፋ የሁለትዮሽ ግንኙነት የጀመሩት እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር መጋቢት 1976 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም