ቀጥታ፡

ህግ አውጪ፣ አስፈጻሚና ተርጓሚ አካላት የተሰጣቸውን ሃላፊነት በአግባቡ ሊወጡ ይገባል- አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ

አርባ ምንጭ፤ መስከረም 24/2015 (ኢዜአ) ከፍትህ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን ለማቃለል ህግ አውጪ፣አስፈጻሚና ተርጓሚ አካላት በህገ-መንግስት የተሰጣቸውን ሃላፊነት በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ አሳሰቡ።

የጋሞ ዞን አስተዳደር የፍትህ ተደራሽነትን ለማገዝ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቋሚ ችሎት ማስቻያ ህንጻ አበረክቷል፡፡

በዚህ ወቅት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፤ ፍትህ የሚረጋገጠው ህግ አውጪው፣ ህግ አስፈጻሚውና ተርጓሚው በህገ-መንግስት የተሰጣቸውን ሃላፊነት በአግባቡ መወጣት ሲችሉ ነው ብለዋል፡፡

ህግ ተርጓሚው በነጻነት ህግን በአግባቡ መተርጎም፣ ህግ አስፈጻሚው ደግሞ ህጉ በአግባቡ እንዲፈጸም ማድረግ እንዲሁም ህግ አውጪው ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ሰላምና ዕድገት ሊያረጋግጡ የሚችሉ ህጎችን ማውጣት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በሀገራችን አስተማማኝ ፍትህ ለማረጋገጥ የዘርፉ ተቋማት መገንባት እንደሚገባ ያመለከቱት አፈ ጉባኤው፤ የጋሞ ዞን አስተዳደር ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ላበረከተው ቋሚ ችሎት ማስቻያ ህንጻ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በሀገሪቱ ከፍትህ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት የፍትህ አካላት የተሰጣቸውን ሃላፊነት በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት በዚህ መልክ የሚያደርጉት ድጋፍ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አረዳ በበኩላቸው፤ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በየክልሉ እንዲደራጁ ከታወጀ ጀምሮ ላለፉት 18 ዓመታት በክልሎች ተዘዋዋሪ ችሎት እያስቻሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጋሞ ዞን አስተዳደር ያደረገው አስተዋጽኦ የፍትህ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያግዝና አርአያነት ያለው መሆኑን በመግለጽ አመስግነዋል፡፡

ይህን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም የህዝቡን የፍትህ ችግር ለመፍታት አበክረው እንደሚሰሩ አቶ ሰለሞን አስታውቀዋል፡፡

የዞኑ ምክር ቤት የነበረውን ህንጻ በማደስ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ችሎት ማስቻያነት ማበርከታቸውን የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ ባደረጉት ንግግር አረጋግጠዋል።

የተበረከተው ህንጻ ህዝቡ ፍትህ ፍለጋ ወደ ሌሎች አካባቢ በመሄድ ለተለያዩ ወጪና እንግልት ሲዳረግ የነበረውን ችግር በማቃለል ትልቅ እፎይታ ሊሰጥ እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም