የሕግ ታራሚዎችን የአገር ልማት ተሳትፎ ማጠናከር ይገባል

122

መስከረም 23/2015 /ኢዜአ/ የሕግ ታራሚዎች በአገር ልማትና ግንባታ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ በማረሚያ ቤቶች የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የፍትሕ ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ተናገሩ።

የፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን በሥራቸው የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አባላትና አመራሮች እውቅናና የማዕረግ እድገት ሰጥቷል።     

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ በማዕረግ እድገቱ የረዳት ኮሚሽነርነት ማዕረግ ሲሰጣት በርካታ አትሌቶችን በማሰልጠን ለትልቅ ደረጃ ያበቃው አሰልጣኝ ሁሴን ሺቦም የረዳት ኮሚሽነርነት ማዕረግ አግኝቷል።          

ከፍተኛውን ማዕረግ ያለበሱት የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በማረሚያ ቤት ዙሪያ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች ተጠናክረው  ይቀጥላሉ ብለዋል።   

የሕግ ታራሚዎችን በማረም በልማትና የአገር ግንባታ ሥራዎች ላይ ተሳታፊ በማድረግ ሂደት የማረሚያ ቤቶች የላቀ ሚና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።

በማረሚያ ቤቶች የሚገኙ የህግ ታራሚዎች ጥሩ ስነ-ምግባርና የሙያ ክህሎት ይዘው እንዲወጡ መሰራት አለበት ብለዋል።

በፌደራልና በክልሎች የሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ በተቋም ደረጃ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉም ተናግረዋል።   

የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል ዳመነ ዳሮታ በበኩላቸው፤ በሰብአዊ መብት አያያዝ ረገድ ማረሚያ ቤቶች የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በሕግ ጥላ ሥር የሚቆዩ ዜጎች ታንጸው አምራች ዜጋ እንዲሆኑ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።    

ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፤ ለታላቅነት ያበቃኝ የፌደራል ማረሚያ ቤት በዛሬው እለት ደግሞ የማዕረግ እድገት ስለሰጠኝ በእጅጉ ተደስቻለሁ ብላለች።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም