ቀጥታ፡

የአሹራ በዓል በትግራይ ክልል አልነጃሺ መስጊድ በድምቀት ተከበረ

መቀሌ መስከረም 11/2011 በአረቦች ሙሀረም ወር አስረኛው ቀን ላይ የሚከበረው የአሹራ በዓል በትግራይ ክልል ነጋሽ ከተማ በሚገኘው አልነጃሺ መስጊድ በድምቀት ተከበረ። በሂጂራ አቆጣጠር የ1440ኛው የአሹራ በዓል ላይ ኤርትራውያን ጨምሮ በርካታ የስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ተገኝተዋል። ኤርትራዊያን በበዓሉ ላይ ሲታደሙ ከሃያ ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑንም ተመልክቷል። የኤርትራ እስልምና ሃይማኖት ተከታዮችን በመወከል በበዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት  ሀጂ ኡስማን መሀመድ ከበርካታ ዓመታት በኋላ በዓሉን ከኢትዮጵያዊያን ወንድሞቻቸው ጋር ማክበራቸውን ገልጸዋል። ይህም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተጀመረው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ውጤታማ ስለመሆኑ አንድ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አገራቱ ወደሰላም መምጣታቸው በዓሉን ከማክበር በተጨማሪ ለሃያ ዓመታት ያላገኟቸውን ቤተሰቦች ለማግኘት እንዳስቻላቸውም ሀጂ ኡስማን ገልጸዋል፡፡ " በአሁኑ ወቅት የተፈጠረውን ሰላም ለመጠበቅና የሁለቱ አገራት እድገትና ልማት እንዲፋጠን የሃይማኖት አባቶች የበኩላችንን እገዛ ማድረግ አለብን " ሲሉም ገልጸዋል፡፡ በአስመራ ከተማ የሚኖሩት ወይዘሮ ሀዳስ መሀመድ በበኩላቸው ከኢትዮጵያ መንግስት በተመቻቸላቸው ትራንስፖርት ወደአልነጃሺ መስጊድ በመምጣት የአሹራ በዓል ከኢትዮጵያውያን ቤተሰቦቻቸው ጋር በማክበራቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ "ኢትዮጵያዊያንም ሆነ ኤርትራውያን ያለፈውን ታሪክ በመርሳት በሰላም፣ በፍቅርና በአንድነት መኖር አለብን" ሲሉም ገልጸዋል፡፡ ከሚኖርበት ሳዑዲ አረቢያ በመምጣት በዓሉን በሰላምና በፍቅር በማክበሩ መደሰቱን የተናገረው ኤርትራዊው ወጣት መሀመድ ኢብራሂም ነው፡፡ ወጣቶች ፀረ ሰላም ተግባርን ለሚያቀጣጥሉ ኃይሎችና ግለሰቦች መጠቀሚያ ከመሆን ተቆጥበው ለሰላምና ልማት መስራት እንዳለባቸው አመልክቷል። " ከኤርትራ ወንድሞቻችን ጋር የአሹራ በዓል ከሃያ ዓመታት በኋላ በጋራ በማክበራችን ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል" ያሉት ደግሞ የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ዜነብ አደም ናቸው፡፡ የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼክ አደም አብዱልቃድር በበኩላቸው በሁለቱም አገራት ሰላም መፈጠሩ ለፖለቲካ መሪዎች ብቻ ሳይሆን ለሃይማኖት አባቶችና እምነት ተከታዮችም እፎይታ መስጠቱን ገልጸዋል። ሰላምን በዘላቂነት ለማስቀጠል ሥራው ለመንግስት ብቻ የሚተው አለመሆኑን ጠቁመው፣ በሀገራቱ መካከል የተፈጠረው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል፡፡ የአልነጃሺ ታሪካዊ ስፍራ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም እንዲመዘገብና የቱሪስት መስህብ እንዲሆን ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ሼክ አደም ጠይቀዋል፡፡ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ስፍራውን ለማስተዋወቅና ተጨማሪ የምርምር ሥራዎችን ለማካሄድ ቃል መግባቱንም ሼኽ አደም ተናግረዋል፡፡ በአለነጃሺ መስኪድ ትናንት በተከበረው የአሹራ በዓል ላይ ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎችና ከኤርትራ የመጡ 20ሺህ የሚደርሱ የእስልምና እምነት ተከታዮች ተገኝተዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም