ቀጥታ፡

በኢንዶኔዥያ ንግድ ኤክስፖ የሚሳተፉ 40 የኢትዮጵያ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ተመዝግበዋል

ባህር ዳር (ኢዜአ) መስከረም 23/2015 "በመጪው ጥቅምት ወር በኢንዶኔዥያ ጃካርታ በሚካሄደው የንግድ ኤክስፖ ላይ ለመሳተፍ 40 የኢትዮጵያ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት መመዝገባቸውን በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አምባሳደር ገለጹ።

አምባሳደር አልቡስይራ ባስኑር ለኢዜአ እንደገለጹት ሁለቱ አገራት በኢንቨስትመንት፣ በንግድና ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ያላቸው ግንኙነት በፍጥነት እያደገ መጥቷል።

በግንኙነታቸውም በኢንዶኔዥያ የሚመረቱ የኢንዱስትሪ ውጤቶች በኢትዮጵያ ገበያ የሚገቡበትና የኢትዮጵያ ቡና፣ ጥጥና ሌሎች ምርቶችም በኢንዶኔዥያ ገበያ የሚቀርቡበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል።

የኢንዶኔዥያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በጨርቃጨርቅ እና በሌሎች ዘርፎች የሥራ እድል በመፍጠርና ኢኮኖሚውን በማጠናከር አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን አምባሳደሩ ተናግረዋል።

ከኤክስፖው ጎን ለጎንም የኢትዮጵያና የኢንዶኔዥያ ባለሀብቶችና ጉዳዩ የሚመለከተቻው የመንግስት አካላት የሚመክሩበት የንግድ ፎረም እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

"በፎረሙም በሁለቱ አገራት የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ የጋራ ውይይት ይካሄዳል" ብለዋል።

የፎረሙ ዋና ዓላማም በኢትዮጵያ ያለውን እምቅ የኢንቨስትመንት አማራጭ ለኢንዶኔዥያ ባለሀብቶች በማስተዋወቅ በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ማመቻቸት ነው።

ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ባለሃብቶች በኢንዶኔዥያ ከሚገኙ ባለሃብቶች ጋር ትስስር በመፍጠር የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለማስገባትና ምርቶችን በቀላሉ የሚልኩበትን እድል ለመፍጠር ነው።

አራት የኢንዶኔዥያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ዝግጅት ላይ በነበሩበት ወቅት የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ ግንኙነቱ ተቋርጦ እንደነበረ ያስታወሱት አምባሳደሩ፣ ግንኙነቱ ዳግም እንዲታደስ አበክረው እንደሚሰሩም  አረጋግጠዋል።

አምባሳደር አልቡስይራ በዓለም ንግድ ስምምነት ከተደረገባቸው ውጭ ያሉ ምርቶችን ወደ አፍሪካ ለማስገባት በቀጥታ ኢትዮጵያን ተመራጭ የማድረግ ፍላጎት ያላቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

እንቦጭን ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማዋል የሚያስችል የአሰልጣኞች ስልጠና በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዠያ ኢምባሲ ትብብር በባህር ዳር ከተማ መስጠቱን ኢዜአ መዘገቡ የሚታወስ ነው።

የኢትዮ-ኢንዶኔዥያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1961 የተመሰረተ መሆኑን ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም