የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባት ወዳጅነታቸውን ሊያጸኑ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባት ወዳጅነታቸውን ሊያጸኑ ይገባል
መስከረም 23 ቀን 2015 (ኢዜአ) የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባት ወዳጅነታቸውን ሊያጸኑ እንደሚገባ በጄኔቫ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዘነበ ከበደ ተናገሩ።
ኢትዮጵያ ከጥንት እስከዛሬ ያጋጠሟትን ፈተናዎች በህዝቧና በመሪዎቿ ትግልና ጥረት እየረታች ጉዞዋን ቀጥላለች።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ከስልጣን የተወገደው አሸባሪው ህወሃት ክህደት ፈጽሞ ጦርነት ከከፈተ በኋላም ኢትዮጵያ ፈተናዋ ቀጥሏል።
መንግስት ባለፉት ሁለት ዓመታት የሽብር ቡድኑ የደቀነውን የሀገር ህልውና ስጋት የማክሸፍና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ እርምጃ ወስዷል።
በጉዳዩ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በጄኔቫ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዘነበ ከበደ፤ አንዳንድ አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያሳዩት የተዛባ ዕይታ የአገሪቷን እውነታ ያላገናዘበና ሉዓላዊነቷን የሚጻረር መሆኑን ይናገራሉ።
የኢትዮጵያን ህልውና ለማዳከምና ብሎም ለማፍረስ የተነሳው አሸባሪው ህወሃት ከውጭ ሃይሎች የተቀበለውን ተልእኮ ለማሳካት እየጣረ መሆኑን አንስተዋል።
የአሸባሪውን ህልውና ለማስቀጠል በግልጽና በስውር ጭምር ድጋፍ የሚያደርጉ የውጭ አካላት ክፉ ተግባራቸው በፍፁም ሊሳካላቸው አይችልም ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ከጥንትም የውጭ ወራሪን ጭምር በመመከት ለአገራቸው ህልውና ወደ ኋላ እንደማይሉ አስታውሰው አሁንም ሉአላዊነቷን ለማስከበር በጋራ መቆማቸውን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የአሸባሪው ህወሃት አጋዥ የሆኑ የውጭ ሃይሎች ከዚህ በመውጣት የመንግስትን የሰላምና የልማት ጥረት ሊደግፉ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከሁሉም የዓለም ሀገራት ጋር በትብብር የመስራትና ወዳጅነትን ማጠናከርን መሰረት ያደረገ ግልፅ አቋም መሆኑን አምባሳደር ዘነበ ገልጸዋል።
በመሆኑም ይህን የሚያደርጉ አካላት አገር ለማፍረስ የተነሳውን አሸባሪ ቡድን ከመደገፍ እሳቤና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተቆጥበው ከመንግስት ጋር በወዳጅነትና መርህን መሰረት ባደረገ መልኩ እገዛና ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።