ዳያስፖራው የኢትዮጵያን እውነታ ለማስረዳትና የውጭ ጫናዎችን ለመመከት እየሰራ ነው--የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራው የኢትዮጵያን እውነታ ለማስረዳትና የውጭ ጫናዎችን ለመመከት እየሰራ ነው--የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት
መስከረም 23 / 2015 (ኢዜአ) ሶስተኛው ዙር ወረራን ተከትሎ የተፈጠሩ የውጭ ጫናዎችን ለመመከትና የኢትዮጵያን እውነት ለማስረዳት ዳያስፖራው የሚያከናውናቸውን የፐብሊክና ዲጂታል ዲፕሎማሲ ስራዎች ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ገለፀ።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወንድወሰን ግርማ ለኢዜአ እንዳሉት ዳያስፖራው የሀገርን ገፅታ ለመገንባትና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው።
ከዚህ ቀደም አሸባሪው ህወሃትና ጋላቢዎቹ በኢትዮጵያ ህልውና ላይ ጋርጠውት የነበረውን አደጋ ለመቀልበስ በተደረገው ሁሉን አቀፍ ትግል ዳያስፖራው
" #NOMORE በቃ '' ንቅናቄ ያሳየው ዘመቻ የማይረሳ ነው ብለዋል።
በዚህም ዳያስፖራው በሀገሪቱ ላይ ታስበው የነበሩ ጫናዎች እንዲከሽፉና የተሳሳቱ ምልከታዎችም እንዲስተካከሉ ሚናው የላቀ እንደነበር ተናግረዋል።
አሸባሪው ህወሃት ለሶስትኛ ጊዜ የከፈተውን ወረራ ተከትሎ ዳያስፖራው ንቅናቄውን አጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰው፤በመደበኛ መገናኛ ብዙሃን ጭምር የኢትዮጵያን እውነታ ለማሳወቅ እየተሟገተ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አደረጃጀት ጥምረት አባላት ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ቡድን በኢትዮጵያ ላይ ያወጣውን ሪፖርት በመቃወም ለሚመለከታቸው ተቋማት ደብዳቤ መፃፋቸውንም አንስተዋል።
የጥምረቱ አባላት በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ጉዳይን እንዲመረምር የተሰየመው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ቡድን እንዲፈርስ መጠየቃቸውን እንዲሁ።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ከዳያስፖራ አደረጃጀት አመራሮች ጋር በመሆን ዳያስፖራው የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅና ጫናዎችን ለመመከት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን ለማጠናከር እየተሰራ ነው ብለዋል።
ዳያስፖራው በተደራጀ ሁኔታ በአንድነት በመቆም ለሀገሩ የሚያሳየውን አለኝታነት እንዲያስቀጥል የጠየቁት ዳይሬክተሩ፤አገልግሎቱም አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።
ዳያስፖራው ከገፅታ ግንባታ ባለፈ በሀገሪቱ የልማት ስራዎችና ወቅታዊ ሀገራዊ ጥሪዎች ላይ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
በዚህም ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል 500 ሚሊዮን ብር ከዳያስፖራው ለማሰባሰብ ንቅናቄ መጀመሩን በመጠቆም።
በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኢፌዴሪ ኤምባሲ አስተባባሪነት ከአቡዳቢ የኢትዮጵያውያን ኮሚዩኒቲ ማሕበር፣ከኩፖን ሽያጭ፣ ከሚስዮኑ ዲፕሎማቶችና ሠራተኞች ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ገልጸዋል።
ዳያስፖራው እያከናወናቸው ያሉትን የፐብሊክና ዲጂታል ዲፕሎማሲ ተግባራት እንዲሁም የሰብአዊ ድጋፎች አጠናክሮ እንዲቀጥልም ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል።