በክልሉ ለትምህርት መስፋፋት የባለሀብቱና የህበረተሰቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ

105

ሀዋሳ መስከረም 22 /2015 (ኢዜአ) በሲዳማ ክልል ትምህርትን ለማስፋፋት እየተደረገ ባለው እንቅሰቃሴ የባለሀብቶችና የህብረተሰቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ በየነ በራሶ ጥሪ አቀረቡ።

ምክትል ርዕሰ-መስተዳድሩ ጥሪውን ያቀረቡት በቀድሞ ተማሪዎች እና በጎ ፈቃደኞች የመልሶ ግንባታና ዕድሳት የተከናወነለት የቀድሞ አለታ ወንዶ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተመረቀበት ወቅት ነው።   

በቀድሞ የአለታ ወንዶ መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ትብብር ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የትምህርት ቤቱ መልሶ ግንባታና ጥገና ተካሂዶ ተመርቋል።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ በትምህርት ዘርፍ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የትምህርት ተሀድሶ ተነድፎ በዚህ ዓመት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ተገብቷል ብለዋል።

በዚህ እንቅሰቃሴ ላይ እስካሁን አርሶ አደሩና ባለሀብቱ ያሳየው ተነሳሽነትና ተሳትፎ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

የትምህርት ቤቱ እድሳትና ግንባታ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዘሪሁን ቃሚሶ በበኩላቸው 50 ዓመት እድሜ ያለው አንጋፋ ትምህርት ቤት ጥገናና የማስፋፊያ ስራ ሳይሰራለት በመቆየቱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውሰጥ እንዳለፈ ጠቅሰዋል።

አሁን በፈቃደኝነት ከተሰባሰቡ የቀድሞ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በመሰብሰብ እድሳትና ግንባታ መካሄዱን አመላክተዋል።

በዕድሳቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ የ7 ህንፃ ሙሉ ጥገና፣ የመግቢያ በርና አጥር ግንባታ፣ የውሰጥ ለውስጥ መንገድ፣ የተማሪ መቀመጫ ወንበሮችና ጥቁር ሰሌዳ የማሟላት ስራ መከናወኑን ጠቁመዋል።

በቀጣይ ምዕራፍም ለትምሀርት ቤቱ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች፣ ዘመናዊ ቤተ-መጸሐፍት፣ የጥልቅ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራና  ሌሎችንም  ስራዎች ለማከናወን ማቀዳቸውን አሳውቀዋል።

በምረቃ መርሃ-ግብሩ ላይ ለትምህርት ቤቱ  እድሳትና ጥገና አስተዋጽኦ  ላደረጉ  አካላት የከተማ እስተዳደሩ ሰርፊኬትና እውቅና ሽልማት አበርክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም