በክልሉ በግንባታ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ እንዲጠናቀቁ በትኩረት እየተሰራ ነው--አቶ ኦርዲን በድሪ

103

መስከረም 22/2015 (ኢዜአ) በሐረሪ ክልል በግንባታ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በከተማዋ ከ175 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከልና መቆጣጠር የህንጻ ግንባታ ጎብኝተዋል።

በከተማው ፖሊስ ኮሚሽን ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚከናወነው የግንባታ ስራ በፍጥነትና በጥራት እየተከናወነ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ የእሳት አደጋና ሌሎች ተፈጥራዊ አደጋዎች ሲያጋጥም መከላከል የሚያስችል ቴክኖሎጂን መሰረት ባደረገ መልኩ እየተገነባ መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ ለክልሉ ብቻ ሳይሆን ለአጎራባች ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች ጥቅም እንዲሰጥ ተደርጎ በመገንባት ላይ እንደሚገኝ ገልጸው ከሰው ሃይልና ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ግብዓት የማሟላት ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚከናወን ተናግረዋል ።

በክልሉ የከተማ ተቋማዊና መሰረተ ልማት ማስፋፋያ ፕሮግራም (ዩ.አይ.አይ.ዲ.ፒ) ኃላፊ አቶ ፈቲህ ረመዳን በበኩላቸው ግንባታው 24 በመቶ መድረሱንና በተያዘው በጀት ዓመት ሙሉ ለሙሉ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ስራ እንደሚገባ ነው የገለጹት።

በተጨማሪም ርዕሰ መስተዳድር በከተማው ሸንኮር ወረዳ ከ58 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነባ የሚገኘውን የወጣቶች ማዕከልንና ሌሎች የግንባታ ፕሮጀክት ስራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም