የኢሕአፓ ከፍተኛ አመራሮች ነገ አዲስ አበባ ይገባሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢሕአፓ ከፍተኛ አመራሮች ነገ አዲስ አበባ ይገባሉ
አዲስ አበባ መስከረም 11/2011 የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ/ ኢሕአፓ/ ከፍተኛ አመራሮች ነገ አዲስ አበባ ይገባሉ፡፡ የፓርቲው አባልና የአቀባበል ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ መላከ ካሣ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት ኢሕአፓ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እየታየ ያለውን ለውጥ ለመደገፍና የተጀመረው የሠላም፣ የዴሞክራሲና የአንድነት ጭላንጭል እንዳይደበዝዝ የድርሻውን ይወጣል። ለዚህም የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ወደ አገር ቤት ተመልሰው በሠላማዊ መንገድ ለመታገል ወስነዋል ነው ያሉት፡፡ የፓርቲው ዋና ዓላማ በትግል የተገኘውን ልምድ ከነባራዊ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ የትውልዱ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ "ለሕዝብ መብት መሞት አኩሪ ታሪክ ነው" የሚለውን እምነት በተግባር ማሳየትና አርአያ መሆን ነው ብለዋል፡፡ ፓርቲው በትግል መንገዶች ያለፈባቸውን መልካምና መጥፎ የታሪክ ምዕራፎቹን ለወጣቱ በማስተማር ለሕዝብ የገባውን ቃል ኪዳን በመጠበቅ የተሻለች ኢትዮጵያን መገንባት በሚሉና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያይ ገልጸዋል፡፡ የለውጡ ተፎካካሪና የመፍትሄ አካል ለመሆን የፓርቲው አባላት፣ ደጋፊዎቻቸውና ወጣቶች የሚሳተፉበት ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ መንግሥት በተለያዩ አገራት መቀመጫውን ያደረጉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አገር ውስጥ ገብተው በሠላማዊ መንገድ እንዲታገሉ ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ ነው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገር ቤት እየገቡ ያሉት፡፡