ቀጥታ፡

ስራ እድል ፈጠራን ለማጎልበትና የመካከለኛና አነስተኛ ኢንዱስትሪ ልማትን ለማጠናከር የሚረዱ 11 አገር አቀፍ ጥናቶች ይፋ ሆኑ

አዲስ አበባ መስከረም 11/2011 በአገሪቷ የስራ እድል ፈጠራን ለማጎልበትና የመካከለኛና አነሰተኛ ኢንዱስትሪ ልማትን ለማጠናከር የሚረዱ 11 አገር አቀፍ ጥናቶች ይፋ ሆኑ። ጥናቶቹ የተካሄዱት በኢትዮጵያ የልማትና ምርምር ኢንስቲትዩት በኩል ሲሆን በአገሪቷ ባሉ አስር ከተሞች ላይ ተካሄዷል። በጥናቱ መሰረት በተለይም የካፒታልና የመስሪያ ቦታ እጦት በዘርፉ ለማስመዝገብ የታሰበውን ያክል ግቦች እንዳይሳኩ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ነው ተብሏል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዮሃንሰ አያሌው ጥናቱ ይፋ በሆነበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በጥናቱ አጠቃላይ በአገሪቷ ውስጥ ያሉትንና በመካከለኛና አነስተኛ ኢንዱስትሪ ላይ የተሰማሩትን ለመዳሰስ ተሞክሯል። የስራ ፈጠራ ላይ ያላቸውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ  እንዲያስችልም ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ፖሊሲ ለመቅረጽ የሚያግዝ ሆነው የተዘጋጁት  11 ጥናቶች ከሁለት ዓመት በላይ ጊዜ የወሰዱና በአገሪቷ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁሉንም ያቀፉ የዘርፉ አጋዥ ጥናቶች መሆናቸውን  ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የልማትና  ምርምር  ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ሙሉ ገብረየስ በጥናቱ ላይ ከተሳተፉት አጥኚዎች መካከል አንዱ ሲሆኑ፣ ጥናቱ ለዘርፉ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል። በዘርፉ የሚጠበቀውን ያክል ውጤት ያልተመዘገበው ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ስለነበሩ ነው ብለዋል። ያንን ተግዳሮት ለይቶ መፍትሔ ለማስቀመጥ ጥናቱ አጋዥ መሆኑን በማውሳት። በአጠቃላይ ወደ 8ሺህ 174 ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በጥናቱ እንደታዩ ገልጸው፣ በዳሰሳው ወቅትም ከታዩት ችግሮች መካከል የካፒታል፣ የመስሪያ ቦታና የገበያ ትስስር ዋነኞቹ አንደሆኑ ጠቁመዋል። ኢንስቲትዩቱም በጥናቱ የተረጋገጡትን የዘርፉን ተግዳሮቶች ለሚመለከተው የፌዴራል ተቋም በማሳየት ችግሮቹን ለመቅረፍ እንደሚሰራም ተገልጿል። የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ በበኩላቸው፣ ጥናቱ በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ኢንዱስትሪን የሚደግፍና ያሉበትን ችግሮች ለመቅረፍ የሚረዳ ከፍተኛ ግብዓት ነው ብለዋል። በጥናቱ የተደገፈ ስራን መስራት ለዜጎችም ሰፊ የስራ እድል ከመፍጠር አኳያ ላቅ ያለ ሚና እንዳለው ገልጸዋል። ጥናቱ በአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ የሚገኘው የስራ እድል ቀጣይነት ያለውና ዘላቂ የስራ እድል ከመፍጠር አኳያም ሰፊ ዳሰሳ እንዳደረገ ገለጸዋል። የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲም በኢንስቲትዩቱ በኩል በየጊዜው ጥናት የሚያስደረግ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ጥናት በዘርፉ የሚስተዋሉትን ክፍተቶች ለማስቀረት አንዱና ዋነኛው እንደሆነ ተገልጿል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም