በኢትዮጵያ የመጀመሪያው በአዲስ ቴክኖሎጂ ህክምና የሚሰጥ የስትሮክ ህክምና ማዕከል ተመረቀ

273

መስከረም 22/2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የመጀመሪያው በአዲስ ቴክኖሎጂ በመታገዝ የስትሮክ ህክምና መስጠት የሚያስችል ማዕከል መከፈቱን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ማዕከሉን መርቀው በከፈቱበት ወቅት እንዳሉት የጤናው ዘርፍ በርካታ መሻሻሎች እያሣየ ቢሆንም ወደ ፊት ብዙ መሄድ ይጠበቅበታል ብለዋል።

የአክሶል ስትሮክ እና ስፓይን ማዕከል መከፈቱ እንደ ሀገር የስትሮክ ህክምናን አንድ ምዕራፍ ወደ ፊት የሚወስድ መሆኑን ጠቅሰው ማዕከሉ ለዚህ ምረቃ በመድረሱ ያላቸውን አድንናቆት ገልጸዋል።

አዲስ ቴክኖሎጂና የተለየ አገልግሎት ይዞ የመጣ ማእከል በአገሪቱ ለጤናው ዘርፍ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ላለፋት አመታት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና በዚህ ሳቢያ የሚመጣ ሞት እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት ዶክተር ሊያ ችግሩን ለመቅረፍ የጤና ሚኒስቴር ከመከላከል ስራው ጎን ለጎን የስፔሻሊቲ ህክምና አገልግሎት ማስፋፋት ስራ የሚያሰራ የአስር አመት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ እየተተገበረ መሆኑን አመላክተዋል።

መንግስት በመጀመሪያና አጠቃላይ ሆስፒታሎች ኢንቨስት ማድረግ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው የስፔሻሊቲ አገልግሎት ማስፋፋት ላይ የግሉ ዘርፍ ጠንካራ ተሣትፎ እንደሚጠይቅ ነው የጠቀሱት።

ለዚህም መንግስት ለግሉ ዘርፋ ምቹ ሁኔታ የመፍጠርና የማመቻቸት ሥራ እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል።

የአክሶል ስትሮክና ስፓይን ማዕከል አጋር መስራች ዶክተር አከዛ ጠአመ የአክሶል ስትሮክና ስፓይን ማዕከል በሀገራችን አዲስ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑ ለየት ያደርገዋል ብለዋል።

ይህም ለአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከጎረቤት አገራት የሚመጡ ታካሚዎችን የሚያስተናግድ ተቋም መሆኑንም ነው የጠቀሱት።

በአለም ላይ ካለው የስትሮክ በሽታ መጠን ሁለት ሶስተኛው የሚገኘው በታዳጊ ሀገራት መሆኑንና በአምራች እድሜ ክልል ወስጥ ያሉውን የህብረተሰብ ክፍል እያጠቃ እንደሆነ የገለጹት ደግሞ የማዕከሉ አጋር መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ወንድወሰን ገብረ አማኑኤል ናቸው።

ማዕከሉ በድንገተኛ የሚመጡ ታማሚዎችን ተቀብሎ እርዳታ የሚሰጥበት፣ ታካሚዎች በተኙበት ክብደታቸውን መለካት የሚያስችል አልጋ ያላቸው ክፍሎች መመቻቸቱንም አስረድተዋል።

"ካት ላብ" በተባለ መሳሪያም የስትሮክ ህመሙን ከመለየት እስከ ማከም የሚያስችል አገልግሎት በአንድ ማዕከል እንደሚሰጥ ነው የገለጹት።

ማዕከሉ አዲስ ቴክኖሎጂ ባፈራቸው የህክምና መሳሪያዎችና ባለሙያዎች የተደራጀ መሆኑን ተከትሎ ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ በአፍሪካ ሁለተኛ በኢትዮጵያ ደግሞ የመጀመሪያ መሆኑ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም