‘የሆራ ሀርሰዴ’ኢሬቻ በዓል ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲጠናቀቅ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ ነው - አባገዳ ጎበና ኦላ

100

መስከረም 21 ቀን 2015 (ኢዜአ) በነገው ዕለት በቢሾፍቱ ከተማ የሚከበረው ‘የሆራ ሀርሰዴ’ መልካ ኢሬቻ በዓል ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ በሰላም እንዲጠናቀቅ ወጣቶች ሚናቸው መወጣት እንዳለባቸው የቱለማ አባገዳ ጎበና ኦላ አሳሰቡ።

የኦሮሚያ አስተዳደር ቱሪዝም ቢሮ፣ የኦሮሞ አባገዳዎች እና የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር የሆራ አርሰዲ ኢሬቻ በዓል አከባበርን አስመልክቶ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫውም የቱለማ አባገዳ ጎበና ኦላ የሆራ አርሰዴ በዓል ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ በሰላም እንዲጠናቀቅ ወጣቶች ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የኢሬቻ በዓል የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የመተሳሰብ በዓል መሆኑን በመገንዘብ፤ ከኦሮሞ ህዝብ ባሻገር የዓለም ህዝቦች ባህል በመሆኑ ባህላዊ እሴቱን በማስጠበቅ መከበር እንዳለበት አንስተዋል።

ፎሌዎች፣ የመንግስት የጸጥታ አካላት በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከጅምሩ እያከናወኑት የሚገኘው ተግባር የሚመሰገን መሆኑን ጠቅሰው፤ በነገው ዕለት በድምቀት ፈጣሪ የሚመሰገንበት በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ሁሉም የበዓሉ ታዳሚ የጎላ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል።

የሆራ ፊንፊኔ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሚና ለተወጡ የፌደራል፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የኦሮሚያ ፖሊስ እና ሌሎች በጎ ፈቃደኛ አካላት የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም