የአርሶ አደሩን ህይወት በዘላቂነት ለመቀየር የምርምር ተቋማት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል- ዶክተር ይልቃል ከፋለ - ኢዜአ አማርኛ
የአርሶ አደሩን ህይወት በዘላቂነት ለመቀየር የምርምር ተቋማት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል- ዶክተር ይልቃል ከፋለ

ባህርዳር ፤ መስከረም 21/2015 (ኢዜአ) ፡- ምርታማነትን የሚያሳድጉ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን በምርምር በማፍለቅ የአርሶ አደሩን ህይወት በዘላቂነት ለመቀየር የምርምር ተቋማት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ አሳሰቡ።
የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል እያከናወናቸው የሚገኙ የምርምር ስራዎችን በክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ተመራማሪዎች ዛሬ ተጎብኝቷል።
የግብርና ምርታማነት የሚያድገው ከምርምር ማዕከላት አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን በማውጣት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ማድረግ ሲቻል መሆኑን ርዕሰ መስተዳደሩ በወቅቱ ገልጸዋል።
ዛሬ በአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል የተመለከቱት የምርምር ስራዎች የክልሉን አርሶ አደር ምርታማነት ለማሳደግና የዘር አቅርቦት እጥረት ለመፍታት እንደሚያግዙ ተናግረዋል።
ይህም የአርሶ አደሩን ህይወት በዘላቂነት በመቀየር የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት በዘላቂነት ለማሳደግ ለሚደረገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ጅምር መሆኑን ነው ያመለከቱት።
የአርሶ አደሩን የምርጥ ዘር አቅርቦትና የጥራት ችግሮችን በመፍታት ህይወቱን በዘላቂነት ለመቀየር የምርምር ተቋማት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የክልሉ መንግስትም የተመራማሪዎች አቅም እንዲያድግ፣ ተደራሽነቱ እንዲስፋፋ፣ ውጤታማ የምርምር ስራዎች እንዲከናወኑ ከበጀት ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ ያደርጋል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገበ ላለው ለውጥ የምርምር ተቋማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የገለጹት ደግሞ የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጥላዬ ተክለወልድ ናቸው።
የምርምር ማዕከላቱ የጥራት ደረጃቸውን ያሟሉ፣ በሽታን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የሰብልና የእንስሳት ዝርያዎችን በማፍለቅና በማላበድ ለግብርና ምርታማነት ዕድገት የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከልም በዋናነት የብርዕ፣ የአገዳ፣ የጥራጥሬና የድንች ሰብሎችን በምርምር በማውጣት የአርሶ አደሩን የዘር አቅርቦት ችግር እያቃለለ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ማዕከሉ የሚያካሂደውን የምርምር ስራ በማሻሻል የዝርያ ማውጣት ተግባራትን ወደዝርያ ማዳቀል በማሳደግ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅትም ማዕከሉ በበቆሎ፣ ድንች፣ ስንዴ፣ ዳጉሳና ጤፍ ሰብሎች ላይ በዝርያ ማዳቀል ውጤታማ የምርምር ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኃይለማርያም ከፍያለው በበኩላቸው፤ በምግብ ራሱን የቻለ ሀገር ለመገንባት ጠንካራ የምርምር ተቋማት ያስፈልጋሉ ብለዋል።
ትውልድን የሚያሻግር ምጣኔ ሀብት መገንባት የቻሉ ሀገራት በፈጠራ ላይ የተመሰረቱ የምርምር ስራዎችን ባልተመቸ ቦታ ሆነው ሌት ተቀን ቤተ ሙከራ ውስጥ ውለው በማደር ጠንክረው በመስራታቸው እንደሆነ አስረድተዋል።
ዶክተር ኃይለማርያም፤ እኛም ያንን ማድረግ ከቻልን የሀገራችንን ኢኮኖሚ በአጭር ጊዜ በማሳደግ የምግብ ዋስትናችንን ከማረጋግጥ ባለፈ የስነ-ምግብ አመጋገብ ስርዓታችንን ማስተካከል እንችላለን ብለዋል
ለዚህም ተመራማሪዎችም ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተረድተው ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የአርሶ አደሩን ህይወት ሊያሻሽሉ በሚችሉ የምርምር ስራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል ከ60 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ያስገነባውን ባለ3 ወለል ህንፃም ዛሬ አስመርቆ ለአገልግሎት ማመቻቸቱን የኢዜአ ሪፖርተር ከሥፍራው ዘግቧል።