ለወባ በሽታ ተጋላጭ በሆኑ የደቡብ ኦሞ ዞን አካባቢዎች የመከላከል ስራ እየተካሄደ ነው

99

ጂንካ፤ መስከረም 21 ቀን 2015 (ኢዜአ)፡- ለወባ በሽታ ተጋላጭ በሆኑ የደቡብ ኦሞ ዞን አካባቢዎች ህብረተሰቡን ያሳተፈ የመከላከል ስራ እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ።

እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴም 300 ሺህ የአልጋ አጎበር መሰራጨቱ ተጠቁሟል።

የመምሪያው የበሽታ መከላከል እና ጤና ማጎልበት  ዳይሬክተር አቶ ታምራት አሰፋ፤ የአየር መዛባቱን ተከትሎ ባለፉት ሶስት ወራት የወባ ስርጭት በዞኑ ቆላማ አካባቢዎች መከሰቱን ለኢዜአ ተናግረዋል።

የወባ ስርጭቱ ከፍ ብሎ ከታየባቸው አካባቢዎች ዳሰነች፣ኛንጋቶምና ሳላማጎ ወረዳዎች እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል።

በነዚህ ወረዳዎች ቀደም ሲል በሳምንት 800 ያህል ሰዎች በወባ በሽታ ሲጠቃ እንደነበር አስታውሰው፤  ከሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም ወዲህ ባሉት ሶስት ወራት ውስጥ የበሽታው ተጠቂዎች ቁጥር በሳምንት እስከ 2 ሺህ 400 ሰዎች ማሻቀቡን አስታውቀዋል።

ሆኖም የበሽታውን ስርጭት በመከላከል ለመግታት በየደረጃው በተደረገው እንቅስቃሴ እስካሁን በበሽታው ህይወቱ ያለፈ ሰው እንደሌለ ጠቁመዋል።

የበሽታውን ስርጭት በህብረተሰቡ ተሳትፎ ለመከላከል በተደረገው ጥረትም ለወባ ትንኝ መራቢያ ስፍራዎችን የማጽዳት፣ የታቆረ ውሃ የማፋሰስና የማዳፈን   ተግባራት በዘመቻ መከናወኑን ገልጸዋል።

በዞኑ የወባ በሽታ ተጋላጭ በሆኑ ስምንት   ወረዳዎች የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት  የፀረ ወባ ኬሚካል ርጭትና 300 ሺህ የአልጋ አጎበር መሰራጨቱን ጠቁመው በዚህም 230 ሺህ ነዋሪዎችን ከበሽታው መታደግ መቻሉን አስረድተዋል።

የጤና ተቋማት በቅርበት በሌለባቸው ጠረፋማ አካባቢዎች የጤና ባለሙያዎች ቡድን በማሰማራት የወባ በሽታ ምርመራ እና ህክምና አገልግሎት መሰጠቱን አብራርተዋል።

ከምርመራው እና ከህክምና አገልግሎት ባሻገር በአርብቶ አደር አከባቢዎች የአልጋ አጎበር አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም ለማህበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በስፋት እየተሰሩ መሆናቸውን  ነው አቶ ታምራት የተናገሩት።

በወባ በሽታ ተይዘው በጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ህክምና ሲከታተሉ ኢዜአ ያነጋገርናቸው የኛንጋቶም ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ናለፐት አርጎይ በሰጡት አስተያየት ፤ በተደረገላቸው የህክምና እርዳታ ከበሽታው ማገገም እንደቻሉ ተናግረዋል።

የአልጋ አጎበርን በአግባቡ መጠቀም አለመቻላቸው ለበሽታው እንዳጋለጣቸውና በቀጣይ ይህንን በማሻሻል ዳግም ለበሽታው ተጋላጭነታቸውን ለማስቀረት ከሀኪሞች ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም