በክልሉ የተያዘውን የበጋ የስንዴ ልማት እቅድ ለማሳካት በትኩረት ይሰራል

98

ሚዛን አማን፣ መስከረም 21 ቀን 2015 (አዜአ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በዚህ ዓመት የተያዘውን የበጋ የስንዴ ልማት እቅድ ለማሳካት በትኩረት እንደሚሰራ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ገለጹ።

የግብርና ዕድገት ፕሮግራም ምዕራፍ ሁለት ማስጀመሪያ እና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ንቅናቄ ላይ ያተኮረ መድረክ በክልሉ ሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ነዉ።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በመድረኩ ላይ እንዳሉት የበጋ ስንዴ ዕቅድ ለማሳካት ዘርፉን በአግባቡ መምራት ይገባል።

በኢትዮጵያ አሁን እየታየ ያለውን የዋጋ ግሽበት እና የኑሮ ውድነት ለመቀነስ በዋናነት የበጋ ስንዴ ልማት ላይ ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።

በተለይ የበጋ ስንዴን ጨምሮ በትኩረት የሚሰሩ ክልላዊ የግብርና ሥራዎችን ወደ አርሶ አደሩ ቀርቦ የመደገፍ ስራም እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የግብርና ዕድገት ፕሮግራም ምዕራፍ ሁለት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ውስጥ በሚገኙ ስድስት ዞኖች ባሉ 20 ወረዳዎች በ450 ቀበሌዎች እንደሚተገበር ይትገበራል።


ፕሮግራሙ ሴቶችን እና ወጣቶችን የሚያሳትፍ ሲሆን አነስተኛ ይዞታ ባላቸው አርሶና አርብቶ አደሮች አካባቢ ያለውን ስራ ለማሳለጥም ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ባለፉት ስድስት ዓመታት ፕሮግራሙ በተለያየ መልክ ሲተገበር መቆየቱን የተናገሩት አቶ ማስረሻ በቀሪ ጊዜያት ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አስረድተዋል።

የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ በበኩላቸው የግብርና እድገት ፕሮግራም የግብርናውን  ዕድገት ከፍ ለማድረግ ድርሻው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዘርፍ ስኬት ሀሉም ባለድርሻ አካላት ለዕቅዶች ተግባራዊት የበኩላቸውን ሚና መወጣት አለባቸው ነው ያሉት።

የተለያዩ ፕሮጀክቶች ሥራ ሲጀምሩ ሁሉን አቀፍ በማድረግ የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባል ያሉት አቶ ፀጋዬ የግብርና ፕሮግራም ምርትን ለማሳደግ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት አመላክተዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆይው የውይይት መድረክ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዞን ዋና አስተዳዳዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም