ምሩቃን በሚሰማሩበት ውጤታማ ከመሆን ባለፈ ለሀገር እድገትና ሰላም ጠንክረው ሊሰሩ ይገባል----አቶ ኦርዲን በድሪ

ሐረሪ  መስከረም 21/2015 (ኢዜአ) ምሩቃን በሚሰማሩበት የሥራ መስክ ውጤታማ በመሆንና ሕብረ ብሔራዊ አንድነታቸውን በማጠናከር ለአገር እድገትና ሰላም ጠንክረው ሊሰሩ ይገባል ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ አሳሰቡ፡፡

የሃረማያ ዩኒቨርሲቲ ጤናና ሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ በተለያዩ የሕክምና ሙያ ያሰለጠናቸውን ከ500 በላይ ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል115ቱ በሕክምና ዶክትሬት የሰለጠኑ ሲሆኑ ቀሪዎቹ በፋርማሲ፣ በአካባቢ ጤና አጠባበቅ ሳይንስ፣ በአዋላጅ ነርስ፣ በክሊኒካል ነርስና በሌሎች የሕክምና ትምህርቶች የተመረቁ ናቸው።

በምረቃ መርሃግብሩ ላይ የክብር እንግዳ ሆነው የተገኙት የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት፣ ምሩቃን በተሰማሩበት የሥራ መስክና ቦታ ሕብረ ብሔራዊ አንድነታቸውን በማጠናከር ለአገር እድገትና ሰላም ጠንክረው ሊሰሩ ይገባል።

እንደሀገር ከድህነትና ኋላ ቀርነት ለመውጣት ትኩረት መደረጉን የገለጹት አቶ ኦርዲን፣ ከሀዲዎችና የወጭ ጠላቶች ሀገር ለማፍረስ የሸረቡትን ሴራ በማክሸፍ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።   

"ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን አሸባሪው ህወሓት በእብሪት ተነሳስቶ የከፈተውን ጦርነት  በጀግንነት እየመከተ ይገኛል" ያሉት አቶ ኦርዲን፣ ህዝቡ ለሠራዊቱ ደጀንነቱን እያሳያ መሆኑን ገልጸዋል።  

የዛሬው ምሩቃንም ለመከላከያ ሠራዊቱ አስፈላጊው ድጋፍ በማድረግ የደጀንነት ሚናቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

በቀጣይ ወደሥራ ሲሰማሩም ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር በመተዋወቅ ለማህበረሰቡ የተሻለ አገልግሎት በቅንነት መስጠት እንዳለባቸውም ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።

የሃረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል ዩሱፍ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ባለፉት 60 ዓመታት ለአገሪቱ እድገትና የለውጥ ጉዞ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉ ከፍተኛ የትምርት ተቋማት አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ 120 ሺህ የሚጠጉ ምሁራንን አሰልጥኖ ለሀገር ማበርከቱንም ጠቁመዋል።  

ለማህበረሰብ ጤና በሰጠው ትኩረትም ለሕይወት ፋና እስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከፍተኛ በጀት በመመደብ በጤናው ዘርፍ ላይ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

"ተመራቂ ተማሪዎች ሀገራዊ የእድገት ጉዞና የጤና ሴክተር ራዕይ እንዲሳካ ከፍተኛ ሃላፊነት አለባቸው" ያሉት ዶክተር ጀማል፣ በዩኒቨርሲቲው የቀሰሙትን እውቀት ተግባር ላይ በማዋል የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የሃረማያ ዩኒቨርሲቲ ጤናና ሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ ኤክስኪዩቲቭ ቺፍ ዳይሬክተር ዶክተር አህመድ መሃመድ በበኩላቸው "ምሩቃን በተማሩበት ሙያ ያስተማራቸውን ማህበረሰብ በቅንናትና በታማኝነት ሊያገለግሉ ይገባል" ብለዋል።

በሕክምና ሳይንስ ትምህርት ክፍል 3 ነጥብ 74 በማምጣት በማዕረግ የተመረቀውና የወርቅ ሜዳልያ የተሸለመው ዶክተር ጀማል አሊ፣ በሙያው ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ ሀገሩንና ህዝቡን በቅንነት ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

ከሁሉም በላይ የሀገር ሰላምና ደህንነት እንደሚቀድም ገልጾ፣ የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ ሀገራዊ ሃላፊነቱን እንደሚወጣም አረጋግጧል።  

ሰላም ከሁሉም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳዩ እንደሆነና ዜጎችን በቅንነት ለማገልገል መዘጋጀቱን የተናገረው ደግሞ ሌላው ተመራቂ ዶክተር ደረጀው አጋር ነው።

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ እና ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሚስራ አብደላ፣ የጤና ሚኒስቴር ተወካይ ዶክተር ሒሩት ንጋቱ፣ የዩኒቨርሲቲው የሥራ አመራ ቦርድ አባላት እና ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራን እንዲሁም የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።

የሃረማያ ዩኒቨርሲቲ ጤናና ሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ ዘንድሮ ተማሪዎችን ሲያስመርቅ ለ25ኛ ጊዜ ሲሆን ከዛሬ ተመራቂዎች መካከል 26 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም