የስርቆት ወንጀል ሲፈጽም 'እጅ ከፍንጅ' የተያዘ ግለሰብ በ4 አመት ጽኑ እስራት ተቀጣ

283

ነገሌ፣ መስከረም 21 ቀን 2015 (ኢዜአ) በጉጂ ዞን ነገሌ ከተማ በአንድ መድሀኒት ቤት ውስጥ የስርቆት ወንጀል ሲፈጽም 'እጅ ከፍንጅ' የተያዘ ግለሰብ በ4 አመት ጽኑ እስራት መቀጣቱን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ገለጸ፡፡

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የኮሙኒኬሽን ዲቪዥን ሀላፊ ምክትል ኮማንደር በቃሉ በለጠ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ መስከረም 20 ቀን 2015 ዓ.ም ግለሰቡ መድሀኒት የሚገዛ መስሎ በመግባት 2 ሺህ 590 ብር ሲሰርቅ 'እጅ ከፍንጅ' ተይዟል።

ፖሊስ በገንዘብ ስርቆት የጠረጠረውን ጀዋር ዋቆ የተባለ ግለሰብ ላይ ባደረገው ሁለት ሰዓት ያልፈጀ ምርመራ ወንጀሉን አጣርቶ ለፍርድ ቤት ማቅረቡን ገልጸዋል።

የዞኑ የሊበን ወረዳ ፍርድ ቤትም በፖሊስና በዐቃቤ ሕግ ተጣርቶ የቀረበለትን የክስ መዝገብ ተመልክቶ መስከረም 20 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰአት ላይ የቅጣት ውሳኔ ማስተላለፉን ገልጸዋል፡፡

የወንጀል አፈጻጸሙ በገሀድና በቀን የተፈጸመ በመሆኑና ተጨማሪ የሰው ማስረጃ አዳምጦ ግለሰቡን በ4 አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኖበታል ብለዋል፡፡

ግለሰቡ ነገሌ ከተማን ጨምሮ በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር በዘረፋ ወንጀል የሚጠረጠርና በፖሊስ ሲፈለግ እንደነበር አስታውቀዋል።

ፖሊስ እንደየወንጀሉ አፈጻጸም ወዲያወኑ የክስ መዝገቦችን አጣርቶ ለፍርድ ቤት በማቅረብ ውሳኔ የሚያሰጥበት 'አር.ቲ.ዲ' የተባለ አሰራር እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የህግ የበላይነትን ለማስከበር በሚደረግ ጥረት ወንጀለኞች ለጊዜው ይሰወሩ ይሆናል እንጂ ከህግና ከፍትህ መቼም ቢሆን እንደማያመልጡም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም