የኢሬቻ በዓል አከባበርን ይበልጥ በማስተዋወቅ ለቱሪዝም የሚኖረውን ጠቀሜታ ማሳደግ ይገባል -የበዓሉ ታዳሚዎች

132

መስከረም 21 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢሬቻ በዓል አከባበርን ይበልጥ በማስተዋወቅ ለቱሪዝም የሚኖረውን ጠቀሜታ ማሳደግ እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የበዓሉ ታዳሚዎች ገለጹ፡፡

የ2015 ዓ.ም. "ሆራ ፊንፊኔ" ኢሬቻ በዓል ከተለያዩ አካባቢዎች በመጡ የበዓሉ ተሳታፊዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡

በበዓሉም የተለያዩ ብሔረሰብ የተሳተፉ ሲሆን፤ በባህላዊ አልባሳት እንዲሁም በባህላዊ ጭፈራ ደምቆ ተከብሯል፡፡

ኢዜአ በሥፍራው ተገኝቶ ያነጋገራቸው ተሳታፊዎች የገዳ ሥርዓት አካል ሆኖ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የኢሬቻ በዓልን ይበልጥ ለቱሪዝም ጥቅም ማዋል እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

በዚህም በዓሉን ይበልጥ በማስተዋወቅ የውጭ አገራት ዜጎች እንዲጎበኙት ማድረግ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡      

አርቲስት ጋሩማ ሁንዴ፤ በዓሉ የሚከበርበት ቦታን ለጎብኝዎች ምቹ በማድረግ ለቱሪዝም ጥቅም ላይ ለማዋል መስራት እንደሚገባ ይናገራል፡፡    

የኢሬቻ በዓል በአዲስ አበባ በሆቴል እና ንግዱ ዘርፍ ለተሰማሩ ዜጎች ጥሩ የገቢ ምንጭ እየሆነ መምጣቱን የገለጸው አርቲስት ጋሩማ፤ በዓሉን በተገቢው መልኩ በማስተዋወቅ ይህን ይበልጥ ማስፋት እንደሚገባ ተናግሯል፡፡         

ለመጀመሪያ ጊዜ በበዓሉ መሳተፋቸውን የሚናገሩት አቶ ሳሙኤል ይገዙ በበኩላቸው፤ በበዓሉ አከባበር እጅግ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

"እንደዚህ ዓይነቱን ቱባ ባህል ከኢትዮጵያዊያን ባሻገር የመላ አፍሪካዊያን እሴት ማድረግ ይገባል" ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ የበዓሉን አከባበር ይበልጥ ማስተዋወቅ እንደሚገባ በመጥቀስ፡፡    

ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን የመጡት አቶ ደቀቦ ዳሌ፤ በዓሉ የኢትዮጵያዊያን የጋራ እሴት እንዲሆን ስለ በዓሉ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል ይላሉ።   

የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በራሳቸው ቀለም እየታደሙ የባህል ልውውጥ የሚያደርጉበት በመሆኑ ልዩ ገጽታ እንዳለው  ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ በዓሉን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስተዋወቅ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም