የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በአል በሰላም መከበሩን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ

መስከረም 21 ቀን 2015 (ኢዜአ) የ2015 ዓ.ም የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በአል በደመቀና ባማረ ሁኔታ የገዳ ስርአቱን በጠበቀ መልኩ በሰላም መከበሩን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡

ለበዓሉ በሠላም መከበር የድርሻቸውን ለተወጡ አካላት በሙሉ ግብረ ኃይሉ ምስጋና አቅርቧል፡፡

አባ ገዳዎች፣ አደ ስንቄዎች፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመጡ እንግዶች እንዲሁም የውጪ አገር ቱሪስቶች እንደታደሙበት አመልክቷል።

የፀጥታ አካላት ለወንጀልና ትራፊክ አደጋ መከላከልና ምርመራ ተግባራት ተገቢውን ትኩረት በመስጠት አባላትንና አመራሮችን በመመደብ እና በተለይም ህብረተሰቡን አጋዥ በማድረግ ባከናወኗቸው ተግባራት በዓሉን በሰላም ማክበር መቻሉን ገልጿል።

የከተማችን ነዋሪዎች፣ የበዓሉ አስተባባሪዎች፣ በየእርከኑ የሚገኙ የአስተዳደር አካላት የኢሬቻ በዓልን ለማክበር የመጡ እንግዶችን በወንድማማችነትና በእህትማማችነት መንፈስ በማስተናገድ ካከናወኑት ተግባር ባሻገር ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመቀናጀት ለበዓሉ ሰላማዊነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከታቸው በዓሉ ፍፁም ሰላማዊ ሊከበር መቻሉን ጠቁሟል።

የበዓሉ በሰላም መከበር የከተማችንን መልካም ገፅታ ለመገንባት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው በማለት የገለጸው ግብረ ኃይሉ፤ በዓሉ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከበር የድርሻቸውን ለተወጡ አካላት እንዲሁም ድካማቸውን ተቋቁመው ኃላፊነታቸውን በትጋት ለተወጡ መላው የፀጥታ አካላት አባላትና አመራሮች ግብረ ኃይሉ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

በአሉ የሰላምና የደስታ እንዲሆን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብር ኃይል በድጋሚ መልካም ምኞቱን እየገለፀ መስከረም 22 ቀን 2015 ዓ.ም በቢሾፍቱ የሚከበረው የሆራ አርሰዲ የኢሬቻ በአል በተመሳሳይ በሰላም እንዲከበር ህብረተሰቡ ለፀጥታ አካላት የሚያደርገውን እገዛ አጠናክሮ እንዲቀጥል የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል መልእክቱን አስተላልፏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም