ኢሬቻ የሰላምና የወንድማማችነት ምልክት!

59

የኦሮሞ ህዝብ በአንድነት የሚያከብረው ልዩና የማንነቱ መገለጫ የሆነው ኢሬቻ የምስጋና፣ የሰላምና የወንድማማችነት ምልክት ነው፡፡

በኦሮሞ ሕዝብ ባህል ዘንድ ኢሬቻ የሚከበረው ዝናብን፣ ሰላምን፣ ምርት እና የትውልድን ቀጣይነት የሚሰጥ ፈጣሪ በመሆኑ ጤናንና በረከትን የሚችረው እሱ 'ዋቃ' ወይም ፈጣሪ በመሆኑ ምስጋና ለማቅረብ ነው።

ኢሬቻ ፈጣሪን በአንድነት ለማመስገን ታስቦ የሚከወን የህብረተሰቡ የጋራ እሴት በመሆኑ የበአሉ ታዳሚዎች ከየ አቅጣጫው ወደ ስፍራው ተጉዘው በዓላቸውን አክብረውና አመስግነው የሚመለሱበት ታላቅ ዕለት ነው፡፡

ኢሬቻን የተመለከቱ ሰነዶች እንደሚያትቱት የገዳ ስርዓት አንዱ አካል የሆነው ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ በረጅም ጊዜ የሕይወት ውጣ ውረድ ፈጣሪውን የሚያመሰግንብት ባህል፣ ማንነት፣ ስርዓትና ልምድ ነው።

ኦሮሞ የሚያምነው በምንም ነገር የማይመስል፣ የሰማይና የምድር ፈጣሪ፣ የሁሉም የበላይ የሆነ አንድ አምላክ አለ ብሎ ነው። ስለዚህም ነው ኦሮሞ በመልካ (በውኃ ዳርቻ) እንዲሁም በተራራ ላይ ወጥቶ አምላኩን የሚያመሰግነው፤ የሚለምነው።

በዓመት ሁለቴ በሚከበረው ኢሬቻ በዓል በአባገዳዎች መሪነት የኦሮሞ ሕዝብ ፈጣሪን የማመስገኛና መመለጃ ዕለት ነው።

የተራራ ኢሬቻ (ኢሬቻ ቱሉ) የሚከበረው የበጋው ወራት አልፎ የበልግ ዝናብ በሚጠበቅበት ወቅት ነው። በዚህም ፈጣሪ ''እርጥበት አትንፈገን፣ ወቅቶች ጊዜያቸውን ጠብቀው ይምጡ፣ የዝናብ ንፋስ ስጠን'' በማለት ይለምናሉ።

የመልካ (የውኃ ዳርቻ) ኢሬቻ የሚከበረው በመስከረም ወር አጋማሽ፣ ከደመራ ወይም ከመስቀል በኋላ ባለው ቅዳሜና እሁድ የሚከበር ነው። ይህም በሆራ ፊንፊኔና በሆራ አር ሰዲ ይከበራል።በዚህም የክረምት ወራት የዝናብ፣ የደመናና፣ የጭቃና የረግረግ ወቅት አልፎ ለፈካው ወራት በመብቃቱ ምስጋና የሚያቀርብበት ነው።

ኢሬቻ ለሰላምና ለእርቅ ትልቅ ስፍራ የሚሰጥ በዓል እንደሆነም ይታመናል። በዕለቱ ሰላም የአምላክ ስጦታ መሆኑ ይነገራል፤ ሰላም ከሁሉም ሀብት በላይ መሆኑም ይገለጻል።

ከዚህም አልፎ የኢሬቻ በዓል ዘመድ አዝማድ የምገናኝበት፤ ተለያይተው የቆዩ ቤተሰቦች የሚታያዩበት ደማቅ የአደባባይ በዓል ነው።  

በዝናባማው ክረምት በጅረቶችና ወንዞች መሙላት ምክንያት ተራርቀው የነበሩ ቤተ ዘመዶች በባአሉ መከበሪያ ቦታ በባህል ልብሳቸው ድምቀው ይገናኛሉ፤ ይጠያየቃሉ።

ኢሬቻ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የሰላምና የአብሮነት ምልክት መሆኑን የጅማ ከተማ አባ ገዳ ሼህ ነኢም ሀሰን ይገልጻሉ።

በአሉ አንድነታችንን የምናጠናክርበት፣ ተሰባስበን የምንኖርባት፤ ምድርን የፈጠረ አምላክን የምናመሰግንበት፤ ሁሉ ሰው በእኩልነትና በፍቅር ተሰባሶቦ የሚያሳልፈው  በአል ነው ብለዋል።

ልጅ አዋቂው ከያለበት ተሰባስቦ አምላኩን የሚያመሰግንበት፤ እርስበርሱ የምገናኝበት መሆኑንም መስክረዋል።

ኢሬቻ ሰላም ነው። ኢሬቻ አንድነትና የመተሳሰብ፤ የመጠያየቅ እንዲሁም የመታረቂያና የመታደሺያ ትልቅ ባህላዊ ምልክታችን ነው ብለዋል።

በጅማ የኒቨርሲቲ የሚዲያና ኮምዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ደመላሽ መንግስቱ የኢሬቻን ባህላዊ እሴት አስመልክተው እንደገለጹት ኢሬቻ በእኩልነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ የሰላምና የወንድማማችነት ምልክት ነው ብለዋል።

በክረምቱ ቤተሰቦችና ዘመድ አዝማድ ለመገናኘት የእርሻና የስራ ወቅት በመሆኑ እንዲሁም በተለያዩ ማህበራዊ ምክኒያቶች ተራርቀው የነበሩ ወዳጆች የአበቦችን መፍካትና የወንዞችን መጉደል ተከትሎ ይገናኛሉ።

በአሉ አባገዳዎችና ታላላቅ የአገር ሽማግሌዎች ለአምላካቸው ምስጋና ያቀርባሉ። መጪው ጊዜ የሰላም፣ የጤናና የበረከት ይሆን ዘንድ በጸሎት ፈጣሪያቸው ለአመቱ በሰላም እንዲያደርሳቸው መልካም ምኞታቸውን የሚገልጹበት ታላቅ እሴት ነው።

ኢሬቻ ከምስጋናና ከወንድማማችነት ባሻገር በህላዊና ጥበባዊ እሴቱ የህብረተሰቡን የአለባበስ፣ የአኗኗርና የመተሳሰብ ባህል የሚያጎላ መሆኑን ዶክተር ደመላሽ ገልጸዋል።

ይህንን ታላቅ ባህላዊ በአል ላይ የህብረተሰቡ ባህላዊ የጥበብ ስራዎች የሚታዩበት በተለይም የባህላዊ አለባበስ ጎልቶ የሚንጸባረቅበት መሆኑን ገልጸዋል።

ኢሬቻ የአንድነት የሰላም እና የወንድማማችነት ምልክት በመሆኑ ከኦሮሞ ህዝብ በተጨማሪ በርካታ ብሄረሰቦች አብረው የሚያከብሩት እየሆነ መሜጣቱን መምህሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም