ፌዴሬሽኑ አምራቹን ኃይል ለአካል ጉዳት እየዳረጉ ያሉ ግጭቶች ሊቆሙ ይገባል አለ - ኢዜአ አማርኛ
ፌዴሬሽኑ አምራቹን ኃይል ለአካል ጉዳት እየዳረጉ ያሉ ግጭቶች ሊቆሙ ይገባል አለ
አዲስ አበባ መስከረም 11/2011 የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን አምራቹን የህብተረተሰብ ክፍል ለአካል ጉዳትና ሞት እየዳረጉ ያሉ ግጭቶች ሊቆሙ ይገባል አለ። ፌዴሬሽኑ በስሩ ከሚገኙ ስድስት ማህበራት ያሰባሰባቸውን ምግብና አልባሳት በመድሃኔዓለም ትምህርት ቤት ለተጠለሉ ከቡራዩና አካባቢው ለተፈናቀሉ ወገኖች ለግሷል። እርዳታ ለማድረግ የተገኙ አካል ጉዳተኞች ለተፈናቃዮች ሃዘናቸውን በመግለጽ ድርጊቱን አውግዘዋል። የፌዴሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ እንዳሉት በአገሪቱ የአካል ጉዳተኞችን ቁጥር ከሚጨምሩ ክስተቶች አንዱ ግጭት ነው። በመሆኑም ህብረተሰቡ ራሱን ለአካል ጉዳትና ሞት ከሚዳርጉ ድርጊቶች ሰከን ብሎ ማሰብ እንዳለበት መክረዋል። እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች ኢትዮጵያ የጀመረችውን አዲስ ተስፋ ወደኋላ የሚመልስ እንዳይሆን "ማውገዝ አለብን ፣ መቃወም አለብን" ሲሉም የድርጊቱን አስከፊነት ገልጸዋል። ህገ-መንግስቱ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሰጠውን በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ የመስራት መብት መንግስት እንዲያስከብርም ጠይቀዋል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ አንድ አገር እንዳለው አስቦ በአንድነት ተከባብሮ እንዲኖርና ምንነቱ ባልታወቀ ግጭት ተሳታፊ በመሆን አካሉን ከማጣት እንዲቆጠብም ጠይቀዋል። ግጭቶች አካል ጉዳተኝነትን የሚያባብሱና በስራ ላይ ያለውን ኃይል የሚቀንሱ ናቸው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ቶፊቅ ሃምዲኑር ናቸው። በመሆኑም በየአካባቢው የሚፈጠሩ ግጭቶች አምራቹን ዜጋ ለተለያየ የአካል ጉዳት የሚዳርጉ በመሆናቸው ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል ብለዋል። ፌዴሬሽኑ ዳቦ፣ ውሃ፣ የንጽህና መጠበቂያ፣ ብርድልብስና ሌሎች ቁሶችን ያካተተ ድጋፍ አድርጓል። በቡራዩና አካባቢው ባለፈው ሳምንት በተከሰተው ግጭት በሰዎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት አደጋ ደርሷል። በመድሃኔዓለም ትምህርት ቤት ተጠልለው የነበሩ ተፈናቃዮች ቁጥር 3 ሺህ 500 ሲሆን 500ዎቹ ወደ መኖሪያቸው መመለሳቸውን አስተባባሪዎች አስታውቀዋል። ተፈናቃዮች በአዲስ አበባ በ15 መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ሲሆን ወደ መኖሪያ ቀያቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።