የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በግብርና ላይ የሚሰሩ ጠንካራ የምርምር ተቋማትን በስፋት መገንባት ይገባል---ቢሮው

6

ባህር ዳር (ኢዜአ) መስከረም 21/2015 የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በግብርና ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ጠንካራ የምርምር ተቋማትን በስፋት መገንባት እንደሚገባ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የክልሉ የሥራ ሃላፊዎችና ተመራማሪዎች የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል እያከናወናቸው ያሉ የምርምር ስራዎችን እየጎበኙ ነው።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሃይለማርያም ከፍያለው በጉብኝቱ ላይ እንደገለጹት የግብርና ምርታማነትን ለማሳዳግና የተሻሉ የሰብል ዝርያዎችን ለማፍለቅ የምርምር ማዕከላት ጠንክረው ሊሰሩ ይገባል።

እንደሀገር የተያዘውን የእድገት ጉዞ ለማፋጠንና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጠንካራ የምርምር ተቋማት በስፋት መገንባት አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።

የምግብ ዋስትናን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማረጋገጥ እንዲቻል ተመራማሪዎች ሙሉ ጊዜያቸውን በምርምር ሥራ ማሳለፍ እንዳለባቸውም ዶክተር ሃይለማርያም አስገንዝበዋል።

እንደሃላፊው ገለጻ የምርምር ማዕከላት ጠንክረው በመስራት የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን አፍልቀው ለአርሶ አደሩ እንዲያስተዋውቁ የክልሉ መንግስት ድጋፍ ያደርጋል።

የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጥላዬ ተክለወልድ በበኩላቸው ኢኒስቲትዩቱ በክልሉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የተለያዩ የሰብል ዝርያዎችን እያወጣ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ሥራዎቹን እያከናወነ ያለው በሰባት ዋና የምርምር ማዕከላትና በስድስት ንዑስ የምርምር ማዕከላት አማካኝነት መሆኑንም አስታውቀዋል።

የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች በአሁኑ ወቅት በአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል በምርምር የተገኙ የድቃይ በቆሎ፣ የዳጉሳ፣ የስንዴ፣ የጤፍ፣ የድንችና ሌሎች የምርምር ሥራዎችን እየጎበኙ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም