የከተሞች ሴፍቲኔት ፕሮግራም አፈጻጸም ቅንጅት እንደሚጎድለው አንድ ጥናት አመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
የከተሞች ሴፍቲኔት ፕሮግራም አፈጻጸም ቅንጅት እንደሚጎድለው አንድ ጥናት አመለከተ
አዳማ መስከረም 11/2011 ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ ነዋሪዎችን ለመደገፍ በሀገሪቱ የተጀመረው የከተሞች ሴፍቲኔት ፕሮግራም አፈጻጸም የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሠራር ዝቅተኛ መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ፡፡ የጥናቱ ውጤት የቀረበው የፌዴራል የሥራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በአዳማ ከተማ ባካሄደው ሀገር አቀፍ መድረክ ነው። የኢትዮጵያ ዜና አገልገሎት ኤጀንሲ ባካሄደው በዚሁ ጥናት ላይ እንደተመለከተው ከ2008 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው ፕሮግራም ለውጥ እያመጣ ቢሆንም የመንግስታዊ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሠራርና ተሳትፎ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተመልክቷል። የቢራዚል፣ የታይላንድና የቻይና ስኬታማ ተሞክሮዎችን በማሳያነት ያቀረበው የኢዜአ ጥናት፤ በተናጠል ከመንቀሳቀስ ይልቅ የተጠናከረ ጥምረት መፍጠር ኘሮግራሙን ለማሳካትና የከተሞችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ያግዛል። የጠንካራ ድጋፍና ክትትል ክፍተት ፣ የሥራ ቁሳቁስና የጤና መድህን ሽፋን አለመኖር፣ የቀን ክፍያ ማነስ፣ የብድር አቅርቦት ዝቅተኛነት፣ ወርሃዊ ክፍያ በወቅቱ ያለመፈጸም፣ የአቅም ውስንነትና የአመለካከት ማነቆዎች ሌላው በጥናቱ የተመላከቱ ጉድለቶች ናቸው፡፡ ያም ሆኖ በፕሮግራሙ የሚታቀፉ ተጠቃሚዎችን በአግባቡ ከመለየት እና የተዘረጉ የሥራ ዘርፎችን ውጤታማ ከማድረግ አኳያ የተሰራው ሥራ አበረታች እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በቅንጅት የተጀመሩ ሥራዎችን ወደፊት በማራመድ፣ ያልተሰሩና ያልተጠናከሩ የከተማ ግብርና፣ የሥራ ዘርፎችን በአግባቡ የመለየት፣ እንዲሁም ካለሥራ የሚባክነውን ጉልበት መጠቀሙ ውጤታማነትን የሚጨምር በመሆኑ አመራሩ ከወዲሁ ትኩረት ሊያደርግበት እንደሚገባ ጥናቱ አሳይቷል፡፡ የጥናቱ ዓላማ የከተሞች ሴፍቲኔት ፕሮግራም ያስገኛቸው ውጤቶችና በክፍተቶቹ ላይ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለማመላከት እንደሆነ በጥናቱ ተብራርቷል፡፡ ኢዜአ በዘርፉ ያካሄደው ጥናት በመሬት ላይ ያለውን እውነታና የተከናወኑ ሥራዎችን ጭምር በትክክል የዳሰሰ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአዲስ አበባ የሥራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አሳምነው ጌራወርቅ ናቸው። በጥናቱ የተቀመጡ ጠንካራ ጎኖችን ለማስቀጠልና ድክመቱን ለማሻሻል በቀጣይነት በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል። የፌዴራል የሥራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘነበ ኮሞ በበኩላቸው ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በ11 ከተሞች ሴፍቲኔት ፕሮግራም ሲካሄድ መቆየቱን ጠቅሰው፤ በዚህም ከ440 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች በቀጥታ ድጋፍና በልማት ተሳትፈው ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል። አቶ ዘነበ እንዳሉት እካአሁን በፕሮግራሙ አማካኝነት ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ጥቅም ላይ ውሏል፤ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ደግሞ በቁጠባ ተሰብስቧል። "በኢዜአ የተካሄደው ጥናት የተመዘገቡ አበረታች ውጤቶችንና ያሉብንን ክፍተቶች በሚገባ ያመላከተ ነው" ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ከተጠቃሚዎች የቀን ክፍያ ማነስ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ችግር በቅርቡ መፈታቱን ጠቁመዋል። አሁን በጥናቱ እንደ ክፍተት የተቀመጡት የተከታታይ ድጋፍና ክትትል ማነስ፣ የግብዓት አቅርቦትና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡