በክልሉ ጦርነቱን ከመመከት ጎን ለጎን ለወጣቶች ሥራ ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት የተቀናጀ ድጋፍ ያስፈልጋል - ዶክተር ይልቃል ከፋለ

256

ባህር ዳር፣ መስከረም 20 ቀን 2015 (ኢዜአ) በአማራ ክልል አሸባሪው ህወሓት የከፈተውን ጦርነት ከመመከት ጎን ለጎን ለወጣቶች ሥራ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የተቀናጀ ድጋፍ ያስፈልጋል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ተናገሩ።

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ከስራና ክህሎት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ጋር ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተወያይተዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ በውይይት ላይ እንዳሉት፤ አሸባሪው ህወሓት በከፈተው አገር የማፍረስ ጦርነት የአማራ ክልል ለተደራራቢ ችግር ተዳርጓል።

ጦርነቱን ለመቀልበስ እየተደረገ ባለው ርብርብ ክልሉ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰው፤ "ይህም የሥራ ዕድል ፈጠራን ከማስፋት ጀምሮ ሌሎች የልማት ሥራዎችን በአግባቡ ለማከናወን እንቅፋት ፈጥሯል" ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት የከፈተውን ጦርነት ለመመከት የሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት በክልሉ በጀት ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳረፉንም ገልፀዋል።

''በዚህም የተነሳ በክልሉ የወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራን ጨምሮ ሌሎች እንሰራቸዋለን ብለን ያሰብናቸው የልማት ፕሮጀክቶች ባሰብነው ልክ መስራት አልቻልንም፤ ይሄ ትልቅ ተግዳሮት ነው" ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች መረጋጋት እንዳይኖር በሽብር ቡድኖች እየተደረገ ያለው ጫና ከፍተኛ እንደሆነም አብራርተዋል።

የሽብር ቡድኑ ክልሉ ተረጋግቶ ወደ ልማት እንዳይዞር እያደረገ ያለው ጥረት የስራ እድል ፈጠራን ጨምሮ ሌሎች የልማት ስራዎች በአግባቡ እንዳይከናወኑ እንቅፋት መሆኑን አስረድተዋል።

ክልሉ ካሉበት መሰረታዊ ችግሮች አንዱ የሥራ እድል ፈጠራን በታቀደው ልክ ማስኬድ አለመቻል እንደሆነ ገልጸው፤ ለዚህ ደግሞ በርካታ ተቋማት በአሸባሪው ቡድን ዘረፋና ውድመት የደረሰባቸው መሆኑን እንደአንድ ምክንያት ጠቅሰዋል ።

የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ከዚህ በፊትም ለክልሉ በርካታ ድጋፎችን ማድረጉን አስታውሰው፤ ነገር ግን ችግሩ ከተደረገው ድጋፍ በላይ በመሆኑ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

May be an image of 1 person, sitting and standing

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው፣ የአማራ ክልል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖም በስራ እድል ፈጠራ ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ዛሬ ከክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር የተደረገው ውይይት ዓላማ "እኛ ያስፈልጋል የምንለውን ብቻ ሳይሆን ክልሉ ምንድን ነው የሚፈልገው፣ ከኛ ተልዕኮ አኳያስ ምን ያስባል የሚለውን በጋራ ለመመካከር ነው" ብለዋል።

የክልሉ አመራር በአስቸጋሪ ሁኔታም ውስጥ ሁኖ እየሰራ ያለው ስራ እንደሚያስመሰግን ጠቅሰው፤ አመራሩን መደገፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም