በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መክፈቻ ጨዋታዎች ወልቂጤ ከተማና ባህር ዳር ከተማ ድል ቀናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መክፈቻ ጨዋታዎች ወልቂጤ ከተማና ባህር ዳር ከተማ ድል ቀናቸው
መስከረም 20/ 2015 (ኢዜአ) ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መክፈቻ ጨዋታዎች ወልቂጤ ከተማና ባህር ዳር ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን በድል ጀምረዋል።
ፕሪሚየር ሊጉ ዛሬ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ተጀምሯል።
በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ አምበሉ ጌታነህ ከበደ በ50ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ድንቅ የቅጣት ምት ጎል አርባምንጭ ከተማን 1 ለ 0 አሸንፏል።
በሌላኛው ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ ከመመራት ተነስቶ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በድጋሚ የተመለሰውን ኢትዮ-ኤሌትሪክን 2 ለ 1 አሸንፏል።
ዱሬሳ ሹቢሳና ተስፋዬ ታምራት ለጣና ሞገድ ግቦቹን ከመረብ አሳርፈዋል። ስንታየሁ ዋለጩ ለኢትዮ-ኤሌትሪክ ብቸዋን ግብ ያስቆጠረ ተጫዋች ነው።
የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት መርሐግብር በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ቀጥሎ ሲውል በነገው ዕለት ከቀኑ 7 ሰአት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደገው ኢትዮጵያ መድን ከአምናው የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ይጫወታል።
እንዲሁም ከቀኑ 10 ሰአት ድሬዳዋ ከተማ ከሲዳማ ቡና ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ከነገ በስቲያ ከቀኑ 7 ሰአት ወላይታ ድቻ ከኢትዮጵያ ቡና፤ ሐዋሳ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፎውን ከሚያደርገው ለገጣፎ ለገዳዲ ከቀኑ 10 ሰአት ላይ ይጫወታሉ።
የዘንድሮው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር መርሐ ግብሮች በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም(ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ሳምንት)፣በድሬዳዋ ስታዲየም (ከስድስተኛ እስከ 10ኛ ሳምንት) እና በአዳማ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩንቨርስቲ ሜዳ(ከ11ኛ እስከ 15ኛ ሳምንት) ይከናወናሉ።