ኢዜአ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

160

መስከረም 20 ቀን 2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።

ሁለቱ አንጋፋ ተቋማት የተፈራረሙት በትምህርትና ስልጠና፣ በሚዲያና ኮሙኒኬሸን መረጃ ተደራሽነት፣ እንዲሁም ሀገርን አሻጋሪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት ነው።

May be an image of 2 people and people standing

የኢዜአ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሠይፈ ደርቤ ከተመሰረተ 80 ዓመታትን ያስቆጠረው ኢዜአ፤ በ38 ቅርንጫፎቹ ዜና እና ዜና ነክ ስራዎችን በሀገር ውስጥና በውጭ ቋንቋዎች ተደራሽ እያደረገ ነው ብለዋል።

ኢዜአ በ2022 ዓ.ም በአፍሪካ ተጠቃሽ የዜና ምንጭ ለመሆን ያስቀመጠውን የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ለማሳካት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር መስራቱ ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የሙያ መስኮች የተማረ የሰው ኃይልን ለሀገር ያበረከተ አንጋፋ ተቋም እንደሆነ ገልጸው፤ የሚዲያና ኮሚኒኬሸን ዘርፍም ለዚህ ጉልህ አብነት ነው ብለዋል።

የትብብር ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት ከዚህ ቀደም ያላቸውን ትብብር ይበልጥ በማጠናከር የሀገር ግንባታ ተልዕኳቸውን በአግባቡ ለማከናወን እንደሚያስችላቸው አንስተዋል።

በተለይም ኢዜአ የሰነቀውን ራዕይ ዕውን ለማድረግ በትምህርትና ስልጠና ብቁ የሰው ሀብት ለማፍራትና ተቋማዊ አቅሙን ለመገንባት ዕድል እንደሚፈጥርለትም ነው ያብራሩት።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሐና በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የቅድመ ምረቃና የድህረ ምርቃ መርሐ ግብር ተማሪዎች ከንድፈ ሃሳብ ባሻገር የተግባርና የሕይወት ዘመን ክህሎት ስልጠናዎች እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል።

በዚህም በእውቀትና ክህሎት ብቁ ተማሪዎችን ለማፍራት ከተቋማት ጋር በመተባበር በተለያዩ መስኮች የተግባር ልምምድ እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ዛሬ ከኢዜአ ጋር የተደረገው የትብብር ስምምነትም ዩኒቨርሲቲው በጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ በስፋት እየሰራ ያለውን ትምህርትና ስልጠና ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚያስችለው ነው ያነሱት።

ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ሬዲዮ ጣቢያ ባለቤት በመሆኑ በቀጣይ በሚዲያ አቅሙን ለማሳደግ ኢዜአን ከመሰለ አንጋፋ ተቋም ጋር በትብብር መስራቱ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርለት ጠቅሰዋል።

የጥናትና ምርምር ውጤቶች ለህብረተሰቡና ለተቋማት ተደራሽ ሆነውና ተተግብረው የሚፈለገውን ለውጥ እንዲያመጡ በሁሉም የሚዲያ አማራጭ ተደራሽ መሆን እንደሚገባቸው ነው የተናገሩት።

ኢዜአ የሚዲያ ተቋማት የዜና ምንጭ በመሆኑ የዩኒቨርሰቲው ችግር ፈች ጥናትና ምርምር ስራዎችን ጨምሮ ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት የሚበጁ ስራዎችን ይበልጥ ተደራሽ እንዲሆኑ ያስችለዋል ብለዋል።

ተቋማቱ ከስምምነት ባለፈ ሀገር አሻጋሪ በሆኑ ችግር ፈች ጉዳዮች ላይ በትብብር በመስራት ተልዕኳቸውን እንደሚወጡና አሻራቸውን እንደሚያስቀምጡ የተቋማቱ ኃላፊዎች ጠቁመዋል።

ኢዜአ በአዲስ የገነባውን የሚዲያ ኮምፕሌክስ ሕንጻ ወደ ሙሉ ስራ ለማስገባት አስፈላጊ ግብዓቶችን እያሟላ በመሆኑ ሁለቱ ተቋማት ችግር ፈች ሀገራዊ መድረኮችን በጋራ እንደሚያዘጋጁም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም