ቀጥታ፡

ኢሬቻና ሌሎችም መሰል የኢትዮጵያ ባህላዊ እሴቶችን በጋራ ማጉላት ትውልዱን በመልካምነት ለማነጽ ያስችላሉ - ታዳሚዎች

መስከረም 20 ቀን 2015 (ኢዜአ) ኢሬቻና ሌሎችም መሰል የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ እሴቶችን በጋራ ማጉላት ትውልዱን በመልካምነት ለማነጽ እንደሚያስችሉ የኢሬቻ ለሰላም ፎረም ታዳሚዎች ገለጹ።

ከገዳ ስርዓት እሴቶች አንዱ የሆነው የኢሬቻ በዓል ዘንድሮ "እሬቻ የሰላምና የወንድማማችነት ተምሳሌት" በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።

የክብረ በዓሉ አካል በሆነውና ዛሬ በሸራተን አዲስ በተዘጋጀው አራተኛው የእሬቻ ለሰላም ፎረም ላይ የተሳተፉና አስተያየታቸውን  ለኢዜአ የሰጡ  የህብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉት፤ መሰል ባህላዊ እሴቶችን ሁሉም እንደራሱ አድርጎ ካጎለበተው ትውልድን በመልካምነት ለመገንባት ያስችላሉ።

የገዳን ስርዓት እሴቶች አንዱ ስለሆነው ኢሬቻ ምንነት በማንሳት ገለጻቸውን የጀመሩት የፎረሙ ተሳታፊና የደቡብ ክልል ባህልና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሃይለማርያም ተስፋዬ ናቸው።

ከገዳ ስርዓት እና ከኢሬቻ  እሴቶች  ተሞክሮችን በመውሰድ የራሳችንንና በጋራ የማጎልበቱ ስራ በስፋት እየተሰራበት ነው ብለዋል።

ሌላው የበዓሉ ታዳሚና የቀድሞ የአትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ  ወርቁ ጋዲሳ በበኩሉ፤ የሲዳማን ጨምበላላ፣ የወላይታን ጊፋታ፣ የጋሞን ዮ-ማስቃላና  መሰል የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ እሴቶች የእኛ ብለን በጋራ ማጉላት  ከሀገራችን አልፎ ለጎረቤት ሀገራትና ለሌሎችም መትረፍ የሚችሉ መልካም እሴቶች ናቸው ብሏል።

"ኢትዮጵያ የብዙ ሀብቶች ባለቤት ናት" ያሉት ደግሞ የበዓሉ ተሳታፊና የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል አቶ ጋቶች ዎር ናቸው።

ታዋቂው አርቲስት ጌታቸው ሃይለማርያም በበኩሉ፤  እያንዳንዱን ባህላዊ እሴቶቻችንን የእኛ ነው ብለን ካጎላናቸው፣ መተጋጋዝና ማበር ቢቻል ከሌላው ዓለምን ልቀን ልንሄድ እንችላለን ብሏል።

የኢሬቻ በዓል ነገ  በሆራ ፊንፊኔ አዲስ አበባ፤ እሁድ ደግሞ በሆራ አርሰዲ ቢሾፍቱ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም