ቀጥታ፡

የአምራች ኢንተርፕራይዞችን አቅም ለማሳደግ በፋይናንስና መስሪያ ቦታ አቅርቦት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው

መስከረም 20 ቀን 2015 (ኢዜአ) የአምራች ኢንተርፕራይዞችን የማምረት አቅም ለማሳደግ በፋይናንስና መስሪያ ቦታ አቅርቦት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ገለጸ።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት በዘርፉ በሚስተዋሉ ተግዳሮቶችና ቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።

የኢትዮጰያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ብሩ ወልዴ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት የኢንተርፕራይዞች የማምረት አቅም ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው።

በተለይ የማምረቻ ሼዶችን፣የብድር አቅርቦትን ለማመቻቸት እንዲሁም የኢንተርፕራይዞች የመበደር አቅምን ለማሳደግ ደንብ የማሻሻል ስራ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

በተጨማሪም የኢንተርፕራይዞችን የማምረት አቅም ለማጎልበት፣በጥራት እንዲያመርቱና ከሀገር ውስጥ ገበያ ባሻገር ምርታቸውን በስፋት ወደ ውጭ የሚልኩበት ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለአብነትም ባለፈው በጀት ዓመት የኢንተርፕራይዞችን የፋይናንስ ውስንነት ለመቅረፍ የሚያስችል የ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር መመደቡን ተናግረዋል።

ኢንተርፕራይዞች በኢንደስትሪ ፓርኮች ውስጥ ገብተው ማምረት እንዲችሉ ከሰባት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በተለያዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የማምረቻ ሼዶች እየተገነቡ መሆኑንም አቶ ብሩ አመልክተዋል።

በተጨማሪም ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ ለአምራች ኢንተርፕራይዞች የማሽነሪና ሌሎች ግብዓቶች በሊዝ ለማቅረብ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በማምረቻ ቦታ፣ በሃይል አቅርቦት፣ ውሃና መንገድን ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶች ለማሟላት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው ኢንተርፕራይዞች የሰለጠነ የሰው ሃይል እንዲኖራቸው ለማስቻል በሙያ ስልጠና በትኩረት መሰራት አለበት ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም