ለኢሬቻ በዓል ሰላማዊ ክንውን ከፖሊስ ጋር በትብብር የሚሰሩ በርካታ በጎፈቃደኞች ተሰማርተዋል- በጎፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን

141

መስከረም 20/2015(ኢዜአ)በመዲናዋ ለሚከበረው የኢሬቻ በዓል ሰላማዊ ክንውን ከፖሊስ ጋር በትብብር የሚሰሩ በርካታ በጎፈቃደኞች መሰማራታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሕብረተሰብ ተሳትፎና በጎፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ገለጸ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና የበጎፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን የበዓሉን አከባበርና አጠቃላይ የጸጥታ ሁኔታ በሚመለከት ከበጎፈቃደኞች ጋር ተመካክረዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የሕብረተሰብ ተሳትፎና በጎፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ጀማሉ ጀንበር፤ የኢሬቻ በዓል ፍፁም ሰላማዊ በሆነ እና ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

በመሆኑም ለበዓሉ ሰላማዊ ክንውን ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ተቀናጅተው የሚሰሩ በርካታ በጎፈቃደኞች መሰማራታቸውን ተናግረዋል።

የእንቁጣጣሽና የመስቀል በዓላት አከባበር ላይ በጎፈቃደኞቹ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በመቀናጀት አስደናቂ ተግባር ማከናወናቸውን አስታውሰው በኢሬቻም ለተመሳሳይ ሥራ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ከኢትዮጵያ ሃብትነት ባለፈም የዓለም ቅርስ የሆነው የኢሬቻ በዓል እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር የሁላችንም ትብብርና ተሳትፎ ወሳኝ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በበዓሉ አከባበር ሂደት የበጎፈቃደኞች ዋነኛ ተግባር የጸጥታ ሥራዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ማገዝ፣ እንግዶችን ማስተናበርና የመንገድ አቅጣጫዎችን ማመላከት መሆኑን ዶክተር ጀማሉ ተናግረዋል።

በበዓሉ አከባበር ሂደት የተከለከሉ አርማዎችንና ቲሸርቶችን እንዲሁም ግጭት ቀስቃሽ ባነሮችን መያዝ የማይቻል በመሆኑ የቁጥጥር ሥራው የሁላችንም ይሆናል ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር ፋሲካ ፋንታ፤ በዓሉን ስናከብር ሰላማችንን በመጠበቅ ትብብርና አንድነታችንን በማጠናከር መሆን አለበት ብለዋል።

በመዲናዋ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል አከባበር ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በጎፈቃደኞችና አጠቃላይ ማኅበረሰቡ ከፖሊስ ጋር ተባብሮ እንዲሰራ ጠይቀዋል።

በጎፈቃደኞች በበኩላቸው፤ በተሰጣቸው አቅጣጫ መሰረት የጸጥታ ችግር እንዳያጋጥም እና በእንግዶች ላይ እንግልት እንዳይፈጠር ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በመሥራት የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

የኢሬቻ በዓል ቅዳሜ በአዲስ አበባ እንዲሁም እሑድ በቢሾፍቱ የሚከበር ይሆናል።

የኢሬቻ በዓል በዓለም የማይዳሰስ የሰው ልጅ ቅርስነት ኢትዮጵያ ካስመዘገበቻቸው ቅርሶች የገዳ ሥርዓት አካል መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም